FDRE Ministry of Agriculture

አርብቶአደሮችን፣ የቁም እንስሳት ላኪዎችን እና ኤክስፖርት ቄራዎችን ያገናኘ ፕሮጀክት

ያቤሎ፣ ሚዚያ 18/2018 ዓ.ም (ግብርና ሚኒስቴር) የግብርና ሚኒስቴር የአደጋ ስጋት ቅነሳና አካታች የኢኮኖሚ እሴት ማሻሻያ ፕሮጀክት የአርብቶአደሩን ሕይወት ለማሻሻል እየሰራ ይገኛል።

ፕሮጀክቱ በ3 ክልሎች ከፍተኛ የእንስሳት አቅርቦት ባላቸው አካባቢዎች 18 የእንስሳት ማቆያ ማዕከላትን ለመገንባት ግብ ጥሎ እየሰራ ሲሆን 7ቱ ተጠናቀው ለተጠቃሚዎች ተላልፈዋል፤ ቀሪዎቹ በቅርቡ ይጠናቀቃሉ።

ፕሮጀክቱ በኦሮሚያ ክልል በቦረና ዞን ያስገነባቸውን የእንስሳት ማቆያ ማዕከላት (Livestock Collection Center) የፌደራልና የክልል ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ለተጠቃሚ ማህበራት አስረክቧል።

በግብርና ሚኒስቴር የአደጋ ስጋት ቅነሳና አካታች የኢኮኖሚ እሴት ማሻሻያ ፕሮጀክት ብሔራዊ አስተባባሪ ጀማል አልይ በርክክብ ሥነ ሥርዓቱ ላይ እንደገለጹት፣ የእንስሳት ማቆያ ማዕከላት ዋና ዓላማ በአርብቶአደሩ ዘንድ ያለውን የእንስሳት ግብይት ስብራት በመጠገን ተጠቃሚ ማድረግ ነው።

ማዕከላቱ አርብቶአደሩን በግብይት ቀጥተኛ ተሳታፊ በማድረግ በዝቅተኛ ዋጋ እንዳይሸጥ ከማገዛቸው ባሻገር ለቄራዎች፣ ለሥጋ እና ቁም እንስሳት ላኪዎች የጎላ አስተዋጽኦ ያበረክታል ብለዋል።

እንስሳቱ ሳይጉላሉ በአንድ ቦታ አሰባስቦ የገበያ ትሥሥር ለመፍጠር የእንስሳት ማቆያ ማዕከላቱ የጎላ አስተዋጽኦ እንደሚኖራቸው ብሔራዊ አስተባባሪው ጠቁመዋል።

የኦሮሚያ ክልል መስኖና አርብቶ አደር ምክትል ቢሮ ኃላፊ ሮባ ቶርጨ በክልሉ 6 የእንሥሳት ማቆያዎች ለመገንባት ታቅዶ 3ቱ ተገንብተው ለአገልግሎት ዝግጁ መሆናቸውን ገለጸው፣ ማቆያዎቹ እንስሳትን በአንድ ቦታ በማሰባሰብ ነጋዴውና አርብቶአደሩ የሚገናኙበት ድልድይ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የአርብቶ አደሩን ሕይወት ለመቀየር ማህበራት የተረከቧቸውን የእንስሳት ማቆያዎችን በአግባቡ ለአገልግሎት እንዲያውሉ አቶ ሮባ አሳስበዋል።

የኦዳሮባ አርብቶአደሮች ኅብረት ሥራ ዩኒየን ሥራ አስኪያጅ መስፍን አለማየሁ በበኩላቸው አርብቶአደሮች እንስሳቱን ወደ ሞጆ እና አዳማ በማጓጓዝ በዝቅተኛ ዋጋ ለመሸጥ ይገደዱ ነበር ተናግረዋል።

የአደጋ ስጋት ቅነሳና አካታች የኢኮኖሚ እሴት ማሻሻያ ፕሮጀክት የቁም እንስሳት ማህበራትን፣ ላኪዎችንና እርብቶ አደሩን ለማገናኘት የእንስሳት ማቆያዎችን በመገንባቱ ማህበረሰቡን የሀብቱ ተጠቃሚ ያደርጋል።

የእንስሳት ማቆያ ማዕከላቱ በውስጣቸው በረት (የከብት፣ የፍየል፣ የግመል)፣ የመኖ ማከመቻና መሸጫ፣ ሚዛን፣ የከብት መጫኛ (Loading Rump)፣ የእንስሳት ጤና ኬላና ሌሎች አገልግሎቶችን ይሰጣሉ።

ዘጋቢ፦ ባህሩ ሰጠኝ

ፎቶግራፈር፦ ማቲዎስ ተገኝ