————————————-
በኢትዮጵያ አርብቶና ከፊልአርብቶአደሩ ሰፊ የእንስሳት ሀብት ባለቤት ነው፡፡ ከዚህ ሃብት ተጠቃሚ እንዲሆን ምርትና ምርታማነትን ከማሻሻል ባለፈ የተሳለጠ የገበያ ትስስር መፍጠር ይገባል፡፡ ይህን ለማሳካት በግብርና ሚኒስቴር የአርብቶአደር የምግብና ስርዓተ-ምግብ ደህንነት ማሻሻያ ፕሮጀክት (BRENFONS) የቁም እንስሳት ገበያ ማዕከላትን ተደራሽነት እያስፋፋ ይገኛል፡፡

በዚህ ሂደት ተጠቃሚ ከሆኑ የአርብቶአደር አካባቢዎች መካከል በደቡብ ኦሞ ዞን የምትገኘው የማሌ ወረዳ አጆ ቀበሌ አንዷ ናት፡፡ በወረዳዋ የሚገኙ አርብቶአደሮች ሰፊ የእንስሳት ሃብት ባለቤት ሲሆኑ ሃብታቸውን ለገበያ በማቅረብ ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ የገበያ ተግዳሮት ነበረባቸው፡፡
ይህ ችግር ግን አሁን ተቀርፏል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ በወረዳዋ አጆ ቀበሌ በአርብቶአደር የምግብና ስርዓተ-ምግብ ደህንነት ማሻሻያ ፕሮጀክት አማካኝነት የተገነባው የአጆ ቁም እንስሳት ገበያ ማዕከል ነው፡፡
አማካይ አቴ የኢርቦ ቀበሌ ነዋሪና አርብቶአደር ሲሆን የሚያረባቸውን ከብቶች ለገበያ ያቀርብ የነበረው በርካታ ኪሎ ሜትሮችን በመጓዝ ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት ከብቶቹን ባገኘው ዋጋ ስለሚሸጥ ተጠቃሚነቱ እምብዛም ነበር፡፡ ከዚህ ባለፈ በተደጋጋሚ ለፀሃይና ለእንግልት ሲዳረግ ቆይቷል፡፡
የአጆ የቁም እንስሳት ገበያ ማዕከል መገንባት ግን ለአርብቶአደር አማካይ አጎራባች ቀበሌ በመሆኑ አገልግሎቱን በቅርበትና በምቾት ማግኘት አስችሎታል፡፡ “እኛ ወደ ገበያው ሳይሆን ገበያው ወደ እኛ መጣ’’ የሚለው ወጣቱ አርብቶአደር፣ ከዚህ በፊት ተበታትነውና በዛፍ ጥላ ስር የነበሩ የእንስሳት ገበያዎችን ተስማሚ ወደ ሆነ አንድ ማዕከል በመምጣቱ የቁም እንስሳዎቻችንን ተረጋግተን በጥሩ ዋጋ እየሸጥን ነው ብሏል፡፡
የቁም እንስሳት ገበያ ማዕከሉ እንስሳትን ከመሸጥና ከመግዛት ባለፈም የእርስ በእርስ ማህበራዊ ግንኙነታቸውን እያጠናከረላቸው ነው፡፡
ኮከብ ቢንጋ የቁም እንስሳት ነጋዴ ሲሆን ነዋሪነቱ ደግሞ በአጎራባቿ ባላ ቀበሌ ነው፡፡ ተበታትኖ የነበረው የቁም እንስሳት ገበያ ከብቶቹን ለመምረጥ አስቸጋሪ እንደነበረና በዚህ ሂደትም ለፀሃይና ለዝናብ ስለሚዳረጉ የንግድ ፍላጎቱ ቀንሶ ነበር፡፡ የአጆ የቁም እንስሳት ገበያ ማዕከል መገንባት ግን ድካማቸውን ከመቀነሱም ባሻገር የእንስሳት አቅርቦቱን እንደጨመረላቸውም ነግሮናል፡፡

እንዲሁም የማዕከሉ መገንባት የቁም እንስሳት መጥፋትና ስርቆትንም አስቀርቷል፡፡
የአካባቢው አርብቶአደር ከ20-30 ኪሎ ሜትር እየተጓዘ ግብይት ይፈፅም እንደነበር የተናገሩት የአጆ ታዳጊ ማዘጋጃ ቤት ስራ አስኪያጅ አይሰማ አጫ፣ የገበያ ማዕከሉ መገንባት አርብቶአደሩንና ነጋዴውን በቀጥታ ግብይት ስለሚያገናኛቸው ሁለቱም አካላት ተጠቃሚ ከማድረግ ባለፈ ለመንግስት ገቢ በመሰብሰብ ለማህበረሰቡ የመሰረተ-ልማት ጥያቄዎች ምላሽ መስጠት የሚያስችል አሰራር አለ ብለዋል፡፡
የቁም እንስሳት ገበያ ማዕከሉ የአጎራባች ዞኖችንና ክልሎችን ትኩረት እየሳበ በመሆኑ በቀጣይ የማስፋት ስራ ይሰራል፡፡
አዘጋጅ፡- ተዋበ ጫኔ
ፎቶግራፈር፡- ዮዲት እንዳለው