የንብ ተፈጥሮአዊ ተልዕኮ ማር ማምረት ብቻ ሳይሆን የተፈጥሮ ሚዛንን በማስጠበቅ የእፅዋት ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ ነው፡፡ በተጨማሪም ንቦች የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥና የስራ እድል በመፈጠር ኢኮኖሚን ለመገንባት አስተዋፅኦዋቸው የጎላ ነው። ከሌማት ትሩፋት ጋር ተያይዞ እንደ ሀገር ለዘርፉ በተሰጠው ትኩረት የንብ ማነብ ስራ በስፋት በአርሶ አደሩ ዘንድና በከተሞችም ጭምር እየተስፋፋ ሲሆን ይህን ፍላጎት ለሟሟላት በንብ ሀብት ልማት ላይ በርካታ ስራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ፡፡

ከነዚህ ስራዎች ውስጥ የእናት ወይም የንግስት ንብ እርባታ አንዱ ሲሆን በክልሎች የአርሶ አደር ማሰልጠኛ ማህከላትን በመክፈት አርሶ አደሮችን በማሰልጠንና በማዕከሉ ንግስት ንቦችን አባዝቶ ለአርሶ አደሩ በማከፋፈል ሰፊ ስራ እየተሰራ ነው፡፡ ለዚህም በሲዳማ ክልል ከንግስት ንብ ብዜት ጋር በተያያዘ እየተሰራ ያለው ስራ ማሳያ ነው፡፡በሲዳማ ክልል የንብ ማነብ ስራ ዘመናዊ እንዲሆን አርሶ አደሮችን በማሰልጠኛ ማዕከላት በማሰልጠን የተባዙ እናት ንቦችን በማሰራጨት ጥሩ ስራ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው አሁን ላይ እንደ ክልል 108 የንብ ማነቢያ መንደር በማቋቋም በ20 አርሶ አደሮች በማደረጃት የኤክስቴንሽን አገልግሎት እንዲያገኙ እየተደረገ ነው፡፡ በዚህም በርካታ አርሶ አደሮች ንብ በማነብ ኢኮኖሚያቸውን እያሻሻሉ ይገኛሉ፡፡በሲዳማ ክልል ሸበዲኖ ወረዳ የአላአን ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር አለሙ ባራሞ በጓሮአቸው የንብ ማነብ ስራን እየሰሩ ሲሆን 54 ቀፎዎች ላይ ንብ በማነብ ከፍተኛ ተጠቃሚ መሆን ችለዋል፡፡

አርሶአደሩ እንደነገሩን ወደዚህ ስራ ከገቡ ሁለት ዓመት ሲሆናቸው በፊት ከባህላዊ አንድ ቀፎ በአንድ ግዜ ቆረጣ እስከ 6 ኪሎ ግራም ብቻ ነበር የሚገያኙት፡፡ ነገር ግን በማሰልጠኛ ማዕከላት የሚሰጠውን ስልጠና ተከታትለው ወደ ዘመናዊ ቀፎ ከተሸጋገሩ በኋላ ምርታማ መሆን ችለዋል፡፡ በዚህም ከአንድ ቀፎ በአንድ ግዜ ቆረጣ እስከ 18 ኪሎ ማር ያገኛሉ፡፡ በዚህም አንድ ኪሎ ማር እስከ 1 ሺህ ብር በመሸጥ ቤተሰባቸውን በጥሩ ሁኔታ እየደጎሙ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡በተመሳሳይ አርሶ አደር ማጃ ማሞ በጓሯቸው 58 ቀፎዎች ያሏቸው ሲሆን በማሰልጠኛ ማዕከላት በተሰጠው ስልጠና ታግዘው የንግስት ንቦችን በማዘዋወር እያባዙ የማር ምርታቸውን በማሳደግ ለገበያ አቅርበው ተጨማሪ ገቢ በማግኘት ተጠቃሚ መሆን ችለዋል፡፡
