ብሔራዊ የገጠር መሬት መረጃ ስርዓት ዲጅታል ኢትዮጵያ 2030 ዕውን ለማድረግ የበኩሉን አስተዋፅዖ እያበረከተ ይገኛል፡፡
የገጠር መሬት መረጃ ስርዓትን ለማዘመን ባለፉት አምስት ዓመታት በርካታ ስራዎች ተሰርተዋል፡፡ ከነዚህም ውስጥ የአርሶ አደሩን ማሳ በብሔራዊ የገጠር መሬት መረጃ ስርዓት ውስጥ ማስገባትና ከፋይዳ መታወቂያ ጋር ማስተሳረር ለአብነት ተጠቃሽ ናቸው፡፡

ብሔራዊ የገጠር መሬት መረጃ ስርዓት በሀገር አቀፍ ደረጃ በ10 ክልሎች ውስጥ በ536 ወረዳወች እየተተገበረ ይገኛል፡፡ በዚህም 36 ሚሊዮን ማሳ በመለካት ለ34.7 ሚሊዮን ማሳ ይዞታ ማረጋገጫ ምስክር ወረቀት በማዘጋጀት ለ10.8 ሚሊዮን ባለይዞታዎች ተሰጥቷል፡፡
ከባለይዞታዎቹ ውስጥ 32.8 ሚሊዮን ማሳዎችን ወደ ገጠር መሬት መረጃ ስርዓት ማስገባት ተችሏል፡፡

ባጠቃላይ ለመሬት ይዞታ ማረጋገጫ ከተመዘገቡት ባለይዞታዎች ውስጥ 81 በመቶ ያህሉ ይዞታዎች በሴቶች በግል ወይም ከባሎቻቸው ጋር በጋራ የተመዘገቡ ናቸዉ። ይህም የሴቶችን መብትና ተጠቃሚነትን በማረጋገጥ አካታች፣ ፍትሐዊና ዘላቂ የመሬት አስተዳደር ስርዓት ዝርጋታ ትግበራ ማሳያ ነዉ፡፡
ወደ መረጃ ስርዓት በገቡ ማሳዎች ላይ ከ20 በላይ የመሬት ግብይት አይነቶችን አገልግሎት በመስጠት ከ4.6 ሚሊዮን በላይ የመሬት ግብይቶችን ማከናወን ተችሏል፡፡ ይህም ለግብርና ምርትና ምርታማነት ማደግ፣ የባለቤትነት ስሜትን በመፍጠር አርሶ አደሩ መሬቱን እንዲንከባከብ፣ ይዞታዉን ለብድር ዋስትና አሲዞ እንዲበደርና ኑሮዉን እንዲያሻሽል ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ ይገኛል፡፡

የብሔራዊ የገጠር መሬት አስተዳደር መረጃ ስርዓቱ በመዘርጋቱ ዘርፈ ብዙ ስኬቶች የተመዘገቡ ሲሆን ከነዚህም ውስጥ ከ18 በላይ አበዳሪ ተቋማት (ከባንኮችና ማይክሮ ፋይንስ)፣ ከ300 በላይ ቅርንጫፎች የይዞታ ማረጋገጫ ሰርተፊኬትን እንደ ዋስትና በመጠቀም ከ65 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች ከ12 ቢሊዮን ብር በላይ ተበድረዋል፡፡ ከዚህም 5.6 ቢሊየን ብር በጥሬ ገንዘብ እና 6.8 ቢሊዮን ብር የሚገመት የእርሻ መሽነሪዎችን በብድር ተጠቃሚ እንዲሆኑ አስችሏል፡፡ ከነዚህ ተጠቃሚዎች 27 ሺ የሚሆኑት ሴት አርሶ አደሮች ናቸዉ፡፡
በተጨማሪም የዉርስ፣ የስጦታ እና ሌሎች የመሬት ግብይቶች በድጂታል ብሔራዊ የገጠር መሬት መረጃ ስርዓት የተመዘገቡ ሲሆን ተያያዥ ችግሮችንም እየፈታ ይገኛል፡፡
አዘጋጅ፡- ካሳሁን ማለቶ
