(ሆለታ፣ ኅዳር 30 ቀን 2018 ዓ.ም፣ ግብርና ሚኒስቴር)
የእንስሳትና ዓሳ ሴክተር ፕሮጀክት (LFSD) ከእንስሳት ልማት ኢንስቲትዩት እና ከኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር ዝርያቸው የተሻሻሉ 52 ጊደሮችን እና 23 ወይፈኖችን ለአርሶአደሮች አሰራጭቷል።

የፕሮጀክቱ የእንስሳት ዝርያ ማሻሻል ተግባር የእንስሳት ምርትና ምርታማነትን በማሳደግና የሌማት ትሩፋቱን በመደገፍ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል።
የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ፍቅሩ ረጋሳ (ዶ/ር) የእንስሳት ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ 3 ቁልፍ ጉዳዮች (ዝርያ፣ መኖና ጤና) ላይ ርብርብ እየተደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በሰው ሰራሽ ዘዴ የማዳቀል ሥራዎች እየተሰሩ ሲሆን በእንስሳትና ዓሳ ሴክተር ልማት ፕሮጀክት ድጋፍ ዝርያቸው የተሻሻለ ጊደሮች ለአርሶአደሮቹ እየተሰራጩ መሆኑንም ዶ/ር ፍቅሩ ተናግረዋል።
ዘርፉን ለማሻገር ከባህላዊ የአረባብ ዘዴ ወጥተን ቴክኖሎጂን በመጠቀም ዝርያዎችን ማቅረብ ያስፈልጋል ብለዋል።
አርሶአደሮች “ከእጅ ወደ አፍ” የአኗኗር ዘይቤ ወጥተው ከእራሳቸው አልፎ ለገበያ ማቅረብ እንድችሉ የተሻሻሉ ዝርያዎችንና ቴክኖሎጂዎችን ቀኤያቸው ድረስ ተደራሽ ማድረግ እንደሚገባም ሚኒስትር ዴኤታው ተናግረዋል።
የዝርያ ማሻሻል ሥራዎች በምርምር ተቋማት ተጠናክረው ይቀጥላሉ ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፣ በዘርፉ የተሰማሩ ተመራማሪዎች ለአርሶ/አርብቶ አደሩ ዕውቀትና ክህሎትን የማስጨበጥ ሚናቸውን ይወጡ ዘንድ ጥሪ አቅርበዋል።
የእንስሳት ልማት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር አስራት ጤራ በበኩላቸው በ2014 ዓ.ም 500 ሺ የነበረውን የእንስሳት ማዳቀል በ2018 የምርት ዘመን 4.9 ሚሊዮን ለማድረስ ግብ ተጥሎ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
3 ሚሊዮን ዶዝ አባለዘር ለማምረት እየተሰራ መሆኑንም የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ፣ አሁን በሰዓት እየተመረተ ያለውን 30 ሊትር ፈሳሽ ናይትሮጀን ወደ 50 ሊትር ለማሳደግ በግዥ ሂደት ላይ ነው ብለዋል።
በወተት ልማት የተጀመረው የዝርያ ማሻሻል ሥራ ወደ ሥጋ ዝርያ ማባዣ እየተገባ መሆኑንም ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።
ከአሁን በፊት በ7 ማዕከላት 173 ጊደሮችንና 100 ኮርማዎችን ለተጠቃሚዎች ተላልፈዋል በማለት የገለጹት ዶ/ር አስራት፣ 243 አዳቃይ ቴክኒሺያኖችን በማሰልጠን ወደ ክልሎች እያሰማሩ መሆኑንም ተናግረዋል።
የእንስሳትና ዓሳ ሴክተር ልማት ፕሮጀክት ብሔራዊ አስተባባሪ ዶ/ር ቶማስ ቸርነት ኢትዮጵያ በቀንድ ከብት ከአፍሪካ 1ኛ፣ ከዓለም 5ኛ ደረጃ ላይ ብትገኝም የተሻሻሉ ዝርያዎችን ባለመጠቀሟ በቂ ወተትና ሥጋ ማምረት አልቻለችም ብለዋል።
ዶ/ር ቶማስ በገለጻቸው ሴት ብቻ እንድወልዱ የሚያደርግ ቴክኖሎጂ (Sexed Semen) በመጠቀም የዝርያ ማሻሻያ ሥራዎችን ፕሮጀክቱ እየሰራ ይገኛል ብለዋል።
ፕሮጀክቱ የውጭ ዝርያዎችን በማስገባት ከቦረና ዝርያ ላሞች ጋር በማዳቀል ለአርሶ/አርብቶ አደሩ መሰራጨታቸውን ዶ/ር ቶማስ ገልጸዋል።
ፕሮጀክቱ የሌማት ትሩፋቱን በመደገፍ ለአርሶአደሩ የተሻለ የወተት ምርትና ምርታማነትን እያሳደገ ሲሆን አርሶአደሩ ወተት ከማጀት እንዲያገኝ በማድረግ ጤናማ ትውልድ ለመፍጠር የራሱን አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው።
በአጠቃላይ የእንስሳትና ዓሳ ሴክተር ልማት ፕሮጀክት በ4 እሴት ሰንሰለቶች ማለትም (በወተት፣ በሥጋ፣ በዓሳ እና በማር) ውጤቶችን ማሰመዝገቡን ዶ/ር ቶማስ ተናግረዋል።
አርሶአደሮቹ የተሻሻሉ ጊደሮች በማግኘታቸው ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸው ወደ አካባቢያቸው በመውሰድና እንክብካቤ በማድረግ ተጠቃሚ ለመሆን ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።
ዘጋቢ፦ ባህሩ ሰጠኝ
ፎቶግራፈር፦ ተክለመድህን አቻምየለህ
