
ወልቂጤ፣ መስከረም 13/2019 (ግብርና ሚኒስቴር) በግብርና ሚኒስቴር፣ የምርምርና ስልጠና ኢንስቲትዩት እና በሳማኑ (SAMANU) የዘይት አምራች ካምፓኒ ትብብር በሳማኑና በግብርና ዘርፍ ላይ በተሰማሩ ባለሀብቶች መካከል በተደረገው የኮንትራት እርሻ ውል (የአምራች እና አስመራች ውል) መሰረት በኦሮሚያ ክልል ጂማ ዞን በቦቶር ጦላይ ወረዳ በባለሀብቶች እየለሙ የሚገኙ የሱፍ ልማት ማሳዎች የመስክ ምልከታ ተካሂዷል፡፡

በፕሮግራሙ ከፌደራል፣ ከኦሮሚያ እና ከደቡብ ምህራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የመጡ አመራሮች እንዲሁም ከጂማ ዞን የተለያዩ ወረዳዎች የተውጣጡ አርሶ አደሮች በተገኙበት የመስክ ምልከታ የተካሄደ ሲሆን ይህም ለአርሶ አደሮች ስለ ሱፍ ልማት በማስተዋወቅ በስፋት በዘርፉ ተሰማርተው እንዲያለሙ ግንዛቤ መፍጠርን ዓላማ ያደረገ ነው፡፡

በግብርና ሚኒስቴር የሰብል ልማት መሪ ስራ አስፈጻሚ ተወካይ አቶ ተሾመ ገለቱ ከቅባት ሰብሎች ውስጥ ሱፍ በአጭር ግዜ የሚደርስ፣ ለአርሶ አደሩ ገቢ የሚያስገኝና ለምግብ ዘይት ፋብሪካዎች በጥሬ ምርትነት የሚያገለግል እጅግ ተፈላጊ የቅባት ሰብል መሆኑን ጠቅሰው፣ በ2018/19 የምርት ዘመን ከ37 ሺህ ሄ/ር በላይ መሬት በሱፍ ሰብል መሸፈኑን ገልጸዋል፡፡
የሱፍ ልማትን ለአርሶ አደሩ በማስተዋወቅና ስለ አመራረቱ በማሰልጠን የሱፍ ምርትን በስፋት በሀገር ውሥጥ አልምቶ ከውጭ የሚገባውን ለመተካት በግብርናው ዘርፍ ከተሰማሩ ባለሀብቶችና ከዘይት አምራች ካምፓኒዎች እንዲሁም አጋር አካላት ጋር በመተባበር በስፋት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የሳማኑ ከምፓኒ የግብርና ልማት ኃላፊ አቶ ተስፋዬ ሃይሉ በበኩላቸው በየአመቱ የዘይት ጥሬ እቃ ለማስገባት ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ እንደሚወጣ ተናግረው፣ ይህን ምርት በሀገር ውሥጥ ለመተካት ከአርሶ አደሮችና ባለሀብቶች ጋር የውል ስምምነት በመፈጸም የዘር አቅርቦት እያደረጉ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
አሁን ላይ የዘይት ፋብሪካው በቀን እስከ 3 ሺህ 500 ኩንታል የሱፍ ምርት የሚፈልግና የሚመረተው ምርት ከሚፈልገው አንጻር ገና በጅምር ላይ ነው ያሉት ኃላፊው፣ ሁለቱንም አካላት ተጠቃሚ የሚያደረግ ውል በመፈጸም በስፋት ወደዚህ ልማት ለመግባት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በመስክ ምልከታው በኦሮሚያ ክልል ጂማ ዞን በቦቶር ጦላይ ወረዳ ገንደገራንገራ ቀበሌ በ4 ባለሀብቶች በኩታ ገጠም እየለማ የሚገኝ ከ300 ሄ/ር በላይ የሱፍ ልማት ተጎብኝቷል፡፡
ዘጋቢ፡- ካሳሁን ማለቶ
ፎቶ፡- ጌታቸው ምትኩ
