FDRE Ministry of Agriculture

ንብ ማነብ ለአርብቶአደሩ አንዱ የአግሪ ቢዝነስ አማራጭ

——————————

ለአገራችን ግብርና መሰረት የሆነውን አርሶና አርብቶአደር ወደ አገሪ ቢዝነስ ማሻገርና ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ ይገባል፡፡ ለዚህም በአርብቶ አደሩ አካባቢ የግብርና ምርትና ምርታማነትን በዘላቂነት ለማረጋገጥ የአካባቢውን ስርዓተ-ምህዳር እና የአኗኗር ዘይቤን ባገናዘበ መልኩ አግሪ ቢዝነስ እንዲስፋፋ እየተደረገ ነው፡፡ ይህም ለዘላቂ የአርብቶ አደር አካባቢ ግብርና ልማት አንዱ መገለጫ ነው፡፡

አርብቶአደሩ በተለይም ወጣቶችና ሴቶች ከተለመደው የእንስሳት እርባታ ስራ በተጨማሪ በአማራጭ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎች በዋናነትም በአግሪ ቢዝነስ ተሰማርተው ውጤታማ ተሳትፏቸውን እያረጋገጡ ይገኛሉ፡፡

ይህ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ጅምር ተሞክሮዎችን በማስፋፋት ሂደት በግብርና ሚኒስቴር የአርብቶአደር የምግብና ስርዓተ-ምግብ ደህንነት ማሻሻያ ፕሮጀክት (BREFONS) የራሱን ድርሻ እየተወጣ ይገኛል፡፡

በኦሮሚያ ክልል ቦረና ዞን የምትገኘው አሬሮ ወረዳ  በርካታ የእንስሳት ሃብትን ለአገራችን አበርክታለች፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን ወጣቶቿን በማደራጀት በፊት በአርብቶአደሩ አካባቢ ያልተለመዱ አዋጭ የግብርና ልማት ስራዎችን መተግበር ጀምራለች፡፡ የዚህ ማሳያ ከሆኑት መካከል የሜታ ገፈርሳ ቀበሌ አንዷ ናት፡፡

በሜታ ገፈርሳ ቀበሌ የሚገኘው ኤባ ማይክሮ ኢንተርፕራይዝ የማር ምርት ማህበር  7 ሴቶችና 5 ወንዶች በ25 ባህላዊ ቀፎ የተመሰረተ ነው፡፡ ማህበሩ ቀስ በቀስ ስራውን እያስፋፋ አሁን የንብ ማነብን በዘመናዊ ቀፎ ታግዞ እየሰራ ይገኛል፡፡

የማህበሩ ሰብሳቢ ዋቄሹማ ዋቄጋሪ  የማህበሩን የስራ እንቅስቃሴና ተነሳሽነት በማየትየአርብቶአደር የምግብና ስርዓተ-ምግብ ደህንነት ማሻሻያ ፕሮጀክት (BREFONS) 50 ዘመናዊ ቀፎ፣ ሼድ፣ የማር ማጣሪያ፣ ሙሉ የንብ ማነብ ስራ አልባሳት፣ አጥርና ሌሎች አስፈላጊ ግብዓቶችን አሟልቶልን እየሰራን ነው ብሏል፡፡

የማህበሩ አባላት ንቦች በዘላቂነት የሚቀስሙት በቂ አበባ እንዲያገኙ ለማስቻል ዘርፈ-ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ፍራፍሬዎችንና ዛፎችን በመትከል የአካባቢውን ስርዓተ-ምህዳር ጭምር እያስጠበቁ ነው፡፡ 

አለም ወርቁ የማህበሩ ሴት አባል ስትሆን ከጓደኞቿ ጋር በመሆን በአካባቢው ማህበረሰብ ባልተለመደው የንብ ማነብ ስራ ላይ ተሰማርታ ትገኛለች፡፡ የንብ ማነብ ስራ በአካባቢዋ ስለማይተገበር የመስራት እቅዱ አልነበረኝም የምትለው ወጣት አለም፣ ከጓደኞቿ ጋር በመነጋገር ወደ ስራው መግባታቸውን ተናገራለች፡፡

የማር ምርት ስራ በአካባቢው አልተለመደም፤ በተለመደባቸው አካባቢም ሴቶች የማያዘወትሩት ቢሆንም እነ አለም ግን ከወጣት ወንዶች ጋር በመሆን ስራውን በድፍረት ገብተውበት ውጤት ማስመዝገብ ችለዋል፡፡

የማር ምርትና ምርታማነታቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ በመሆኑ በርካታ የአካባቢው ወጣቶች ከእነሱ ትምህርት በመውሰድ ወደ ንብ ማነብ ስራ በስፋት እየገቡ ነው፡፡ አካባቢውም አሁን ከማር ምርት አበርክቶው በተጨማሪ ለአካባቢው ማህበረሰብ የመንፈስ ማደሻ እየሆነ ይገኛል፡፡

አዘጋጅ፡- ተዋበ ጫኔ

ፎቶግራፈር፡- ዮዲት እንዳለው

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *