አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 5/2018 (ግብርና ሚኒስቴር) ጳጉሜን 5 “የነገ ቀን” መርሃ ግብር “ነገን ዛሬ በመገንባት ዲጂታል ሽግግር፣ ሰው ሰራሽ አስተውሎት፣ የምግብ ሉዓላዊነትና ሀገራዊ የአደጋ ሥጋት አስተዳደር ለኢትዮጵያ ማንሰራራት” በሚል መሪ ቃል በሳይንስ ሙዚየም ተከብሯል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ ዲጂታል ሽግግር ምርጫ ሳይሆን የሀገር ሉዓላዊነት ምሶሶ መሆኑን ገልጸው፣ በ2025 (እ.ኤ.አ) ይፋ የሆነው “ዲጂታል ኢትዮጵያ” የመንግስት አገልግሎቶችን ወደ ኤሌክትሮኒክስ በማሳደግ የስኬቶች መሠረት መጣሉን ጠቁመዋል።
እነዚህ ስኬቶች መነሻ እንጂ መዳረሻ እንዳልሆኑና አሁን ከ”ዲጂታል 2025″ ወደ “ዲጂታል 2030” እየተደረገ ባለው ሽግግር ግልጽ አሰራርን በመዘርጋት እና የዜጎችን አለኝታ ማጠናከር እንደሚያስፈልግ አፈ ጉባኤው አስገንዝበዋል።
ቴክኖሎጂው ግብርናን፣ ጤናንና ትምህርትን ጨምሮ ሌሎች ቁልፍ ዘርፎችን በየዕለቱ እየቀየረ መሆኑም ተገለጾአል፡፡

ሰው ሰራሽ አስተውሎት ለኢትዮጵያ ትልቅ ዕድል መሆኑን አፈ ጉባኤው አንስተው፣ ነገር ግን በዚህ ቴክኖሎጂ የሀገራችን ግብ ለማሳካት በኃላፊነት ስሜት መጠቀም እንደሚገባ አሳስበዋል።
በቀጣዮቹ 5 ዓመታት ውስጥ የዲጂታል ሽግግሩ ከስብሰባ አዳራሽ ወጥቶ በአርሶ አደሩ ማሳ፣ በተማሪዎች ክፍል እና በህክምናው ዘርፍ በተጨባጭ አገልግሎት ላይ እንዲውል ባለድርሻ አካላት ርብርብ ማድረግ እንዳለባቸው ጥሪ አቅርበዋል።
የግብርና ሚኒስቴር የፖሊሲ ጥናትና ምርምር መሪ ሥራ አስፈጻሚ ተስፋዬ መንግስቴ (ዶ/ር) በበኩላቸው ድጅታል ሽግግር ከምግብ ሉዓላዊነት ጋር ጥብቅ ቁርኝት ያለው መሆኑን ገልጸዋል።
የገበያ መረጃን ለማዘመን፣ በአየር ንብረት ለውጥ የሚመጡ ተጽዕኖዎችንና የሰብልና የእንስሳት በሽታዎችን ለአርሶ/አርብቶ አደሩ የማስጠንቀቂያ ስርዓት ለመዘርጋት እንዲሁም ፈጣንና ዘመናዊ የግብርና ግብዓት አቅርቦት ለማሳለጥ ድጂታል የላቀ ሚና አለው ብለዋል።
በድጂታል አሰራሮች በአጠቃላይ በግብርና ምርትና ምርታማነት ላይ ለውጦች እየተመዘገቡ መሆኑንም ዶ/ር ተስፋዬ ገልፀዋል።
