FDRE Ministry of Agriculture

ብሔራዊ የአቮካዶ ልማት ፕሮግራም ደረጃቸውን የጠበቁ የአቮካዶ ችግኝ ጣቢያዎችን ለማቋቋም እየሰራ ነው

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 9/2018 (ግብርና ሚኒስቴር) በግብርና ሚኒስቴር ብሄራዊ የአቮካዶ ልማት ፕሮግራም ከኢትዮጵያ ግብርና ባለስልጣን ጋር በመተባበር ፕሮግራሙ ከሚሰራባቸው ክልሎች ለተውጣጡ 64 ከፍተኛ የሬጉላቶሪ እና የፍራፍሬ ልማት ባለሙያዎች ስልጠና ሰጠ።

ፕሮግራሙ ጥራቱን የጠበቀ የአቮካዶ ችግኝ አቅርቦትና ስርጭት ለማረጋገጥ በፕሮግራሙ በታቀፉ ወረዳዎች 30 አዳዲስ የአቮካዶ ችግኝ ጣቢያዎችን በስታንዳርዱ መሰረት ለማቋቋም እና 20 ነባር ችግኝ ጣቢያዎችን ለማሻሻል እየሰራ ነው።   

በግብርና ሚኒስቴር የእርሻና ሆርቲካልቸር ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አማካሪ አሊ መሐመድ (ፕ/ር) አቮካዶ መንግስት ልዩ ትኩረት ከሰጣቸው ፍራፍሬዎች አንዱ በመሆኑ ዘርፉን በስትራቴጂ ለመምራት ብሄራዊ ፕሮግራም ተቀርጾ ወደ ስራ ተገብቷል ብለዋል።

ኢንዱስትሪው እና ዓለም አቀፍ ገበያው የሚፈልገውን የጥራት ደረጃ ለማሟላት ከችግኝ ዝግጅት ጀምሮ እስከ ምርት ድረስ እዕውቅና የሚሰጥበት ዘመናዊ አሰራር እየተዘረጋ መሆኑንም አማካሪው ተናግረዋል።

የብሔራዊ የአቮካዶ ልማት ፕሮግራም አስተባባሪ ተወካይ አቶ ጎሳ ስዩም እንደገለፁት የስልጠናው ዋና ዓላማ በአቮካዶ ችግኝ ጣቢያዎች ያለውን የጥራት ማረጋገጫ ሂደት፣ የመልካም እርሻ አተገባበር፣ የተቀናጀ የተባይና በሽታ ቁጥጥር እና የሆርቲካልቸር ኳራንቲን ሥርዓት ላይ ወጥ የሆነ ግንዛቤ በመፍጠር ጥራቱን የጠበቀ የችግኝ አቅርቦትና ስርጭት እንዲኖር ነው።

ሰልጣኞቹ አዳዲስ የቁጥጥር ስርዓት መስፈርቶችን መነሻ በማድረግ፤ በሀገራዊ የፍራፍሬ ችግኝ ጣቢያ ስታንዳርድ፣ በችግኝ ጣቢያ እና እርሻዎች የምስክር ወረቀት አሰጣጥ ሂደቶች እና ከሬጉላቶሪ ጋር የተያያዙ ጉዳዮች ላይ ሰፊ ግንዛቤ የሚያገኙ መሆኑን አቶ ጎሳ ገልፀዋል፡፡