አዲስ አበባ፣ ሰኔ 5/2018 (ግብርና ሚኒስቴር) ብሔራዊ የአቮካዶ ልማት ፕሮግራም በአቮካዶ ልማት ላይ የሚስተዋሉ የውሃ አቅርቦት እና የድህረ-ምርት ብክነት ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችሉ ዘመናዊ የቴክኖሎጂ ግብዓቶችን ለክልሎች አስረከቧል።

በዛሬው ዕለት በተከናወነው የርክክብ መርሃ-ግብር በአማራ፣ ኦሮሚያ፣ ሲዳማ፣ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ፣ ደቡብ ኢትዮጵያ እና ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልሎች በሚገኙ በፕሮግራሙ በተመረጡ የአቮካዶ ችግኝ ጣቢያዎች ያለውን የውሀ አቅርቦትና አጠቃቀም ለማሻሻል 35 በፀሀይ ሀይል የሚሰሩ የመስኖ ፓምፖች፣ የአቮካዶ ችግኝ ዕድገትን ለማሳደግ ወሳኝ የሆነውን 56 ጥቅል የጥቁር ጥላ መረብ እንዲሁም የአቮካዶ ድራይ ማተር በጠቅላላው ከ69 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ በማድረግ ግዥ በመፈፀም ድጋፍ ተደርጓል፡፡

ብሔራዊ የአቮካዶ ልማት ፕሮግራም አስተባባሪ አቶ አብደላ ነጋሽ የአቮካዶ የመሬት ሽፋንንና ምርታማነትን በማሳደግ የውጭ ምንዛሬ ግኝትን ለማሳደግ እየተሰራ መሆነን ጠቅሰው ድጋፍ የተደረጉ የቴክኖሎጂ ግብዓቶች ለዕቅዱ ስኬት ጉልህ አስተዋዖ እንደሚያበረክቱ ገልፀዋል፡፡

በ15 ዓመት የፕሮግራሙ የቆይታም ከዜጎች ተጠቃሚነት አንፃር ከ3 ሚሊዮን በላይ አነስተኛ አርሶአደሮች፣ 299 አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች፣ 700 ኢንተርፕራይዞች፣ 977,182 ሴቶችና ወጣቶች በፕሮግራሙ በሚፈጠረው የስራ ዕድል ተጠቃሚ ይሆናሉ ብለዋል።

