(አዳማ፣ ታኅሳስ 3 ቀን 2018 ዓ.ም፣ ግብርና ሚኒስቴር)
በኢትዮጵያ የንብ ሀብት ልማት ዘርፉን ለማዘመን ብሔራዊ የንብ ሀብት መረጃ አስተዳደር ስርዓት የተዘጋጀ ሲሆን ይህም የመረጃ መተግበሪያ ላይ የተገነባ ሁሉን አቀፍ ድጅታል ስርዓት (Platform) ነው።

ይህንን የንብ ሀብት ልማት መረጃ አስተዳደር ስርዓት ወደ ሥራ ለማስገባት ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ተደርጓል።
የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ፍቅሩ ረጋሳ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ ለንብ ብሎም ለእንስሳት እርባታ ምቹ ሥነ-ምህዳር ቢኖራትም ዘርፉን በማሳደግ በሚፈለገው ደረጃ ተጠቃሚ መሆነ አለመቻሏን ገልጸዋል።
ዶ/ር ፍቅሩ አክለውም የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር ከተቀረፀ ወዲህ የንብ ሀብቱን በማነቃቃት የማር ምርትና ምርትማነትን ለማሳደግ ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል ብለዋል።
መርሃ ግብሩ ዘርፉን ከማዘመን አኳያ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዘመናዊ ቀፎዎችን ለማሰራጨት እንዳስቻለ ዶ/ር ፍቅሩ ተናግረዋል።
በዚህም በ2017 የምርት ዘመን የማር ምርትን 327 ሺ ቶን ማድረስ የተቻለ ሲሆን በተያዘው በጀት ዓመት ደግሞ 375 ቶን ማር ለማምረት እየተሰራ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

የዓለም አቀፍ የሥነ ነፍሳትና ሥነ-ምህዳር ምርምር ማዕከል (ICIPE-Ethiopia) 135 ወረዳዎችን አቅፎ የመረጃ ስርዓትን በማሻሻል የንብ ሀብታችን እያበረከተ ላለው አስተዋጽኦ ሚኒስትር ዴኤታው ምስጋና አቅርበዋል።
በኢትዮጵያ የዓለም አቀፍ የሥነ ነፍሳትና ሥነ ምህዳር ምርምር ማዕከል (ICIPE-Ethiopia) ዶ/ር ታደለ ተዘራ በበኩላቸው በሽታ ለመከላከል እና የገበያ ሁኔታን በቀላሉ ለማወቅ ጠንካራ የመረጃ ስርዓት መዘርጋት ያስፈልጋል ብለዋል።
የበለጸጉ ሀገራት ከስልጣኔ ማማ የወጡበት ሚስጥር የተደራጀና ፈጣን የመረጃ ልውውጥ ስርዓት መዘርጋታቸው ነው ያሉት ዶ/ር ታደለ፣ የመረጃ ስርዓት የሀሪቱን የንብ ሀብት ለማሳደግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ተናግረዋል።
ዶ/ር ታደለ አክለውም የንብ ሀብት ልማት መረጃ አስተዳደር ስርዓት የንብ እርባታ ምዝገባን፣ የንብ ቀፎዎችን፣ የንብ ውጤቶችን እና የንብ ጤና ቁጥጥርን በማሳደግ ረገድ ጉልህ ሚና ይኖረዋል ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ የንብን ሁለንተናዊ ልማት ለማሳደግ የተመሰረተው ብሔራዊ የንብ ሀብት ልማት መረጃ አስተዳደር ስርዓት ለተመራማሪዎች፣ ለፖሊሲ አውጭዎችና ለሌሎች ባለድርሻ አካላት ታማኝ የመረጃ ማቅረቢያ ሆኖ እንደሚያገለግል ዶ/ር ታደለ ገልጸዋል።

በግብርና ሚኒስቴር የንብና ሐር ልማት ዴስክ ኃላፊ አዝዝ አያሌው የንብ ሀብት ልማት መረጃ አስተዳደር ስርዓት የንብ መኖ ምንጭ ለመከታተል እና ስልጠናን ጨምሮ መረጃን ለማሰባሰብ፣ ለማስተዳደርና ለመተንተን ማዕከላዊ ስርዓት ሆኖ የሚያገለግል የመረጃ ስርዓት መሆኑን ጠቁመዋል።

የንብ ሀብት ልማት መረጃ አስተዳደር ስርዓቱን (APMIS) ከክልሎች ወረዳዎችና ቀበሌዎች ለለተውጣጡ አካላት ተግባራዊ ስልጠና ሲሰጥ መቆየቱን አቶ አዘዝ ተናግረዋል።
መድረኩ የተዘጋጀው የመረጃ ስርዓቱ ያስገኘውን ውጤት ለመገምገምና ለማጽደቅ እንዲሁም በቀጣይ ሥራውን ለማስፋት ነው።
በመድረኩ የተገኙ ባለድርሻ አካላት በተዘጋጀው ብሔራዊ የንብ ሀብት መረጃ አስተዳደር ስርዓት ላይ ገንቢ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

ዘጋቢ፦ ባህሩ ሰጠኝ
ፎቶግራፈር፦ ማቲዎስ ተገኝ
