ግብርናን ከዝናብ ጥገኝነት ለማላቀቅ እና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እንዲሁም በፍጥነት እያደገ የመጣውን ህዝብ የምግብ ፍላጎት ለማሟላት እና የአየር ንብረት ለውጥ አሉታዊ ተጽኖን ለመቋቋም ዘላቂነት ያለው የመስኖ ልማትና የግብርና ውሃ አጠቃቀም ማሻሻል ቁልፍ ጉዳይ ነው፡፡
ባለፉት ዓመታት ዘላቂ የውሃ አጠቃቀምን መሰረት በማድረግ የመስኖ ልማትን ለማስፋፋት ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ በማፍሰስ ማህበረሰቡን ከዝናብ ጥገኝነት እንዲላቀቅ ጥረት ተደርጓል፡፡

በዚህም የተለያዩ ውሀ አማራጮችን በተለያዩ ቴክኖሎጂዎች በመታገዝ የወንዝ ጠለፋ፣ የቅርብ ጥልቀት ዉኃ ጉድጓድና የቤተሰብ ኩሬን በመጠቀም የመስኖ ሰብል ምርትና ምርታማነትን ለማሻሻል የመስኖ ውሃ አቅርቦት ላይ በርካታ ተግባራት በመከናወን ላይ ይገኛሉ።
በአንድአንድ አከባቢዎች አርሶ አደሮች መስኖን ተጠቅመው በዓመት ሦስትና አራት ግዜ በማምረት ተጠቃሚ መሆን ጀምረዋል፡፡
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በጋሞ ዞን አርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳ የላንቴ ቀበሌ ነዋሪ አርሶአደር እስክንድር እያሱ በአንድ ወቅት በእንጨት ሰራ ላይ ተሰማርቶ ሲሰራ ነበር፡፡ ሆኖም በእንጨት ስራው ውጤታማ መሆን እንዳልቻለ ተናግሯል፡፡
ነገር ግን በ2014 ዓ.ም የቀድሞ ስራውን በመተው ወደ መስኖ እርሻ ስራ ገብቶ ውጤታማ መሆን ችሏል፡፡

በዚህም በ5 ሄ/ር መሬት ላይ ሙዝ ፣ ቲማቲም ቃሪያና መሰል ምርቶችን በዓመት ሶስትና አራት ግዜ እያመረተ ጥሩ ገቢ በማግኘት ቤተሰቡን ኑሮ እየለወጠ ይገኛል፡፡
አርሶ አደር እስክንድርና አጎራባች አርሶ አደሮች ይበልጥ ውጤታማ የሚያደርጋቸውን ቴክኖሎጂ በቅርቡ ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡ ይህም በጸሐይ ብርሃን ሃይል (solar energy) የሚሰራ የውሃ መሳቢያ ፓምፕ ሲሆን 40 በመቶን አርሶ አደሮች በማዋጣት 60 በመቶ ደግሞ በመንግስት ድጎማ ተደርጎላቸው በ2017 ዓ.ም ወደ ስራ መግባት ችለዋል፡፡

አርሶ አደሮቹ አሁን ላይ በጸሐይ ብርሃን ሃይል የሚሰሩ የውሃ መሳቢያዎችን ተጠቅመው እያለሙ ሲሆን ምርትና ምርታማነታቸው በመጨመሩ የተሻለ ውጤት እያገኙ ነው፡፡
አርሶ አደር እስክንድር እንዳለው ለናፈጣ የሚያወጣውን ወጭና ለነዳጅ ፍለጋ የሚያባክነውን ግዜ በመቆጠቡ በጣም ውጤታማ ሆኗል፡፡ ለ60 ስራ አጥ ወጣቶችም ቋሚና ግዜያዊ የስራ እድልን መፍጠር ችሏል፡፡
የአርሶና ከፊል አርብቶአደሩን ምርትና ምርታማነት ለማሻሻል ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ተጠቀሚ እንዲሆኑ የማድረጉ ስራ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት፡፡
አዘጋጅ፡- ካሳሁን ማለቶ
ፎቶግራፈር፡- ማቲዎስ ተገኝ