FDRE Ministry of Agriculture

ባለፉት አመታት በተሰሩ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎች 33 ነጥብ 6 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ማልማት ተችሏል፡፡

(አዲስ አበባ፣ የካቲት 19 ቀን 2017 ዓ.ም፣ ግብርና ሚኒስቴር)

በሀገራችን ለእርሻ ስራዎች ከሚታረስ መሬት ላይ በአመት እስከ 130 ቶን አፈር በሄክታር፣ ከገላጣ መሬት ላይ እስከ 300 ቶን አፈር በሄክታር በዓመት እንዲሁም በሁሉም የመሬት አጠቃቀም አይነቶች በአማካይ 42 ቶን አፈር በሄክታር በየዓመቱ እንደሚሸረሸር ጥናቶች ያመላክታሉ።

በዚህም 54 ሚሊየን ሄክታር የሚገመት መሬት የተጎሳቆለና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ መስጠት ከማይችልበት ደረጃም ደርሶ እንደነበር እነዚህ ጥናቶች ምስክር ናቸው።

ይሁን እንጂ ባለፉት ዓመታት በሁሉም የሀገራችን አካባቢዎች በተሰሩ የተለያዩ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎች ከተጎሳቆሉት ቦታዎች ውስጥ 33 ነጥብ 6 ሚሊዮን ሄክታሩን ማልማት ተችሏል፡፡

በግብርና ሚኒስቴር የተፈጥሮ ሃብት ልማት፣ ጥበቃና አጠቃቀም መሪ ስራ አስፈፃሚ ፋኖሴ መኮንን የዘንድሮውን የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ስራዎችን አስመልክቶ በሰጡት ማብራሪያ፣ የዘንድሮ የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ስራ ከጥር 6/2017 ዓ.ም ጀምሮ ለየት ባለ መልኩ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ መጀመሩን አውስተዋል፡፡

በዚህም በዘንድሮው ዓመት 4 ነጥብ 1 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ስራ ለማልማት ታቅዶ ወደ ስራ የተገባ ሲሆን በሁሉም የሀገራችን አካባቢዎች ስራው በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በየአመቱ እንደየክልሎቹ ተጨባጭ ሁኔታ ከ30 እስከ 60 ቀናት አርሶአደሮቹ በየተፋሰሱ እየወጡ የተለያዩ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎችን እንደሚያከናውኑ እንደሆነ ገልፀው፣ በተጎዱ ተፋሰሶች ላይ ከዳር እስከ ዳር በየዓመቱ በአማካይ 14 ሚሊየን የህብረተሰብ ክፍሎችን በማነቃነቅ እንደሚሰራና በዚህም 17 ቢሊዮን ብር በሚገመት የሰው ጉልበት የተለያዩ ስነ-አካላዊ እና ስነ-ሕይወታዊ ስራዎችን በመስራት አሁን ላይ የሚታየውን ለውጥ ማምጣት እንደተቻለም መሪ ስራ አስፈፃሚው አስገንዝበዋል፡፡

በዚህም ባለፉት ዓመታት በተሰሩ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎች የአፈር ለምነትና ጤንነት በመሻሻሉ ምርትና ምርታማነት በከፍተኛ ደረጃ የጨመረበት፣ የደን ሽፋን የጨመረበት እንዲሁም የጠፉ የውሃ አካላት መልሰው የጎለበቱበት መሆኑን አብራርተዋል፡፡

ከዚህ በፊት ተሰርተው በለሙ ተፋሰሶች ላይ ማህበራትን በማደራጀት የንብ ማነብ፣ የእንስሳት ማደለብ እንዲሁም የአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ስራዎችን በመስራት የዕለት ገቢ ከማግኘት ባሻገር ምርቶችን ለውጭ ገበያ ለማቅረብ የሚያስችሉ ስራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡

የተፈጥሮ ሃብት ስራ አመቱን ሙሉ የሚሰራ መሆኑን የገለፁት አቶ ፋኖሴ፣ በቅድመ ዝግጅት ምዕራፍ ወቅትም የተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች፣ ቀያሽ አርሶ አደሮችን ማሰልጠን፣ የአሰልጣኞች ስልጠና መስጠት፣ ተፋሰሶችን የመለየትና ጂኦሪፈረንስ የማድረግ እንዲሁም ሌሎች የቅድመ-ዝግጅት ስራዎችም እንደተሰሩ አስታውሰዋል፡፡

ከዚህም ጎን ለጎን በባለፈው ዓመት የተሰሩ የተፋሰስ ልማት ስራዎችን የማደስ፣ የተተከሉ ችግኞችን የመንከባከብ ስራ፣ የችግኝ ማባዣ ጣቢያዎችን የመከታተል ስራ፣ የችግኝ መትከያ ቦታዎችን የመለየት እንዲሁም የመትከያ ጉድጓዶችን የማዘጋጀት ስራዎች እየተሰሩ እንደሚገኙ ገልፀዋል፡፡

እስከ አሁን በአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ የተከናወኑ ተግባራት በቂ እንዳልሆኑ የተናገሩት መሪ ስራ አስፈፃሚው ከዚህ በኃላም መላው አርሶአደሩንና ህብረተሰቡን፣ የዘርፉን አመራሮችና ባለሙያዎች እንዲሁም የልማት አጋር አካላትን በማቀናጀት የተፈጥሮ ሃብታችንን በመንከባከብና በመጠበቅ የተሻለችና ምቹ የሆነች ሀገር መፍጠር እንችላለን ብለዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ሰለሞን ደምሰው

ፎቶግራፍ፡- ማቲዮስ ተገኝ

#ከማምረትበላይ

#BeyondProduction

—————-