FDRE Ministry of Agriculture

በጥጥ እሴት ሰንሰለት ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን በዘላቂነት በመቅረፍ ምርታማነትን ማሳደግ!

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 11/2018 (ግብርና ሚኒስቴር) ግብርና ሚኒስቴር በጥጥ ልማት እሴት ሰንሰለት ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን በዘላቂነት ለመቅረፍ እንዲሁም ምርታማነትን ለማሳደግ በተጠናው ጥናት ላይ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አድርጓል።

የግብርና ሚኒስቴር ሚንስትር አቶ አዲሱ አረጋ የጥጥ ልማት ዘርፉ ትኩረት ሳይሰጠው በመቆየቱ ማግኘት የሚጠበቅብንን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ሳናገኝ ቀርተናል ብለዋል።

መንግስት ለዘርፉ በሰጠው ትኩረት ከግብዓት አቅርቦት ጀምሮ በጥጥ እሴት ሰንሰለት ላይ የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶችን በዘላቂነት ለመቅረፍ ጥናት መደረጉንም ጠቁመዋል።

የምርምር ማዕከላትን በተለይም የወረር ግብርና ምርምር ማዕከልን በማጠናከር ጥራታቸው የተረጋገጠ የጥጥ ምርጥ ዘሮችን በማውጣትና ተደራሽ በማድረግ ምርታማነትን ማሳደግ እንደሚያስፈልግ ያብራሩት ሚኒስትሩ፣ ጥጥ አብቃይ በሆኑ አካባቢዎች ላይ እውቀት ላይ የተመሰረተ የኤክስቴንሽን ስርዓት ለመስጠትም በትኩረት እንሰራለን ብለዋል።

የግብርና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ደሳለኝ ተሻለ በበኩላቸው በጥጥ ልማት በተለይም በምርጥ ዘር ግብዓት አቅርቦት ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት በትኩረት መስራት እንደሚገባ ተናግረዋል።

የጥጥ ልማት ምርትና ምርታማነት በማሳደግ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ከግብዓት አቅርቦት እስከ ምርት ድረስ ባለው እሴት ሰንሰለቱ ውስጥ የሚስተዋሉትን ተግዳሮቶችን በዘላቂነት ለመቅረፍ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ባላድርሻ አካላት በቅንጅት መስራት አስፈላጊ መሆኑም በውይይቱ ወቅት ተነስቷል።

በጥጥ ልማት እሴት ሰንሰለት ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን በዘላቂነት ለመቅረፍ እና ምርታማነትን ለማሳደግ የተጠናው ጥናትም ቀርቦ በተሳታፊዎች ሰፊ ውይይት ተደርጎበታል።

ዘጋቢ፦ ሰለሞን ደምሰው

ፎቶ፦ ተክለመድህን አቻምየለህ