አርሶአደር ጀማል አህመድ ይባላሉ፡፡ የድሬዳዋ ከተማ ነዋሪ ሲሆኑ ከዚህ በፊት በተለያዩ የንግድ ስራዎች ላይ ተሰማርተው ይሰሩ ነበር። አሁን ግን ብርቱካን፣ ማንጎ፣ ሎሚ እና ሌሎች የፍራፍሬ አይነቶችን እያለሙ ያሉ ሞዴል አርሶአደር ናቸው፡፡

ብርቱካን አሁን ላይ በ12 ሄክታር መሬት ላይ እያለሙ ሲሆን በቅርብ ጊዜ ውስጥም አዲስ 28 ሄክታር መሬት ለማልማት ዝግጅት እያደረጉ ይገኛሉ።
በ12 ሄክታር መሬት ላይ ያለሙትን ብርቱካን ምርቱ ከድሬዳዋ አልፎ ወደ አዲስ አበባ እና ጅግጅጋ ከተማ ለገበያ እያቀረቡ እንደሚገኙ አርሶአደር ጀማል አህመድ ተናግረዋል።
ለወጣቶች የስራ ዕድል ከመፍጠር አንጻር የበኩላቸውን አስተዋፅዖ እያበረኩቱ እንደሚገኙ የተናገሩት አርሶአደር ጀማል፣ አሁን ላይ በጊዜያዊነት ለ220 ወጣቶች እንዲሁም በቋሚነት ለ24 ወጣቶች የስራ ዕድል ፈጥረዋል።

ከከተማ አስተዳደሩ ግብርና ቢሮ የተጠናከረ ሙያዊ ድጋፍና እገዛ እንደሚደረግላቸው የተናገሩት አርሶአደሩ፣ በማሳቸው ላይ በሽታ በተከሰተበት ወቅት ከመድሃኒት ርጭት ጀምሮ የተለያዩ ክትትል እና ሙያዊ እገዛ ይደረግላቸዋል።
የግብርና ልማት ስራ በትኩረት እና በፍቅር ከተሰራ አትራፊና ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ የስራ መስክ መሆኑን ገልጸው፣ የግሉ ሴክተር አልሚዎችም ወደ ልማት ስራው በስፋት ገብተው በማልማት የዘርፉን ምርታማነት ለማሳደግ ብሎም የምግብ ሉዓላዊነታችንን ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት ማገዝ አለባቸው ብለዋል፡፡

አርሶአደር ጀማል በ12 ሄክታር መሬት ላይ እያለሙት የሚገኙት የብርቱካን ማሳ በኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ፣ በግብርና ሚኒስቴር ሚኒስትር አቶ አዲሱ አረጋ እንዲሁም በከፍተኛ የፌዴራልና የክልል የሥራ ኃላፊዎች ተጎብኝቷል።
አዘጋጅ፡- ሰለሞን ደምሰው
ፎቶ፡- ተክለመድህን አቻምየለህ
