FDRE Ministry of Agriculture

በግብርናው ዘርፍ የፋይናንስና ኢንሹራንስ ተደራሽነትን ለማስፋት እየተሰራ ነው

(አዲስ አበባ፣ ሰኔ 4 ቀን 2017 ዓ.ም፣ ግብርና ሚኒስቴር)

ግብርና ሚኒስቴር ዘርፉን ከሚደግፉ አጋር አካላት ጋር በመሆን ለአየር ንብረት ለውጥ ተጋላጭ የሆኑና በአነስተኛ ማሳ የሚያመርቱ አርሶና አርብቶ አደሮችን የፋይናንስ አቅም ለማሳደግ በትኩረት እየሰራ ይገኛል።

በዚህም የገጠር ፋይናንስ ዩኒት በማቋቋም ሚኒስቴር መ/ቤቱ የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ ሲሆን ይህም ተግባር ምርትና ምርታማነትን በመጨመር የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ አይነተኛ ሚና አለው።

በዛሬው ዕለትም በአነስተኛ ማሳ ለሚያመርቱ አርሶና አርብቶ አደሮች የፋይናንስ አቅርቦትን ተደራሽ ማድረግ ላይ ያተኮረ የውይይት መድረክ እየተካሄደ ነው።

በውይይቱም የተለያዩ አጋር አካላት ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎችና ከተለያዩ የአፍሪካ ሃገራት የተውጣጡ የፋይናንስና የግብርና ዘርፍ የስራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል።

የግብርና ሚንስትሩ ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) የተሻሻለው የግብርናና ገጠር ልማት ፖሊሲ አነስተኛ ማሳ ያላቸውን አርሶ አደሮች የፋይናንስ ብድር አቅርቦት እንዲያገኙ ትልቅ ትኩረት እንደሰጠ ተናግረዋል።

መንግስት ለግብርናው ዘርፍ በሰጠው ትልቅ ትኩረት ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ አካታችና የአየር ንብረት ለውጥን መቋቋም የሚያስችል የኢኮኖሚ ማሻሻያ መደረጉንም አስታውሰዋል።

ሃገራችን በአረንጓዴ አሻራ መርሀ-ግብር፣ በመስኖ ስንዴ ልማትና በሌማት ትሩፋት ኢኒሼቲቮች የተገኙ ስኬቶች በምግብ ራስን ለመቻል ለምታደርገውን ጥረት እያገዙ መሆኑንም አብራርተዋል።

የተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም (UNDP) የኢትዮጵያ ተወካይ ሳሙኤል ዲዮ (ዶ/ር) በበኩላቸው የግብርና ፋይናንስና የኢንሹራንስ ወሳኝ ጉዳይ መሆኑን አንስተው፣ ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ ተጋላጭ አርሶና አርብቶ አደሮችን የፋይናንስና የኢንሹራንስ አቅማቸውን የበለጠ እንዲያጠናክሩ ለማድረግ የጀመረችው ተግባር አበረታች መሆኑን ተናግረዋል።

የግብርና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ሶፊያ ካሳ (ዶ/ር) ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ውስጥ ኢትዮጵያ ከ15 በላይ የግብርና ኢንሹራንስ ሞዴሎችን በሙከራ ደረጃ ሲትተገበር መቆየቷን ገልፀዋል።

በአሁኑ ጊዜ ግብርና ሚኒስቴር የገጠር ፋይናንስ ድጋፍ ዩኒት በማቋቋም ዩኒቱ የፋይናንስ፣ የመረጃ እና የግብርና ብድርና ኢንሹራንስ አቅርቦት እና ስርዓቶችን በማስተባበር የሚያገለግል መሆኑንም ተናግረዋል።

ዘጋቢ፦ ሰለሞን ደምሰው
ፎቶግራፍ፦ ማቲዎስ ተገኝ