FDRE Ministry of Agriculture

በግብርናው ዘርፍ የስርዓተ-ጾታ እኩልነት እና ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ እየተሰራ ነው፡፡

በሀገራችን በግብርናው ዘርፍ ሴቶች ከፍተኛ ተሳትፎ ቢኖራቸውም በልፋታቸው ልክ ተጠቃሚ አይደሉም፡፡ በመሆኑም ግብርናን በማዘመን የሚፈለገው ደረጃ ላይ ለማድረስ የሴቶችን ተሳትፎ እና ፍታዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ወሳኝ ነው፡፡

በመሆኑም የሴቶችን እኩልነትና ፈታዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያስችል የስትራቴጂ ሰነድ በማዘጋጀት ወደ ስራ ለማስገባት የግብርና ሚኒስቴር አመራሮች፣ ሰነዱን የገመገሙ የዩኒቨርስቲ ሙሁራንና ባለድርሻ አካላት በተገኙበት የውይይት መድረክ ተካሂዷል፡፡

በግብርና ሚኒስቴር የስራ አመራር ዋና ስራ አስፈጻሚ ተወካይ ጫላ ሆርዶፋ (ዶ/ር ) ግብርና ለሀገር ኢኮኖሚ ከፍተኛ ድርሻን እያበረከተ ያለ ዘርፍ መሆኑን ጠቅሰው ከገጠሩ ማህበረሰብ በግብርናው ዘርፍ ጉልህ ሚና ያላቸውን ሴቶች እኩልነት ማረጋገጥና በልፋታቸው ልክ ተጠቃሚ ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

ይህ በግብርና ዘርፍ የሴቶችን እኩልነትና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተዘጋጀው የስትራቴጂ ሰነድ በሴቶች ተጠቃሚነት ዙሪያ የሚታዩ ችግሮችን በመቅረፍ ጉልህ አስተዋጾ እንደሚያበረክት ያላቸውን እምነት ተናግረው፣ ሰነዱ ዳብሮ የሚፈለገውን ውጤት እንዲያመጣም የሁሉም ባለድርሻ አካለት ተሳትፎ እንዲደረግ ዋና ስራ አስፈጻሚው አሳስበዋል፡፡

በግብርና ሚኒስቴር የፖሊሲ ጥናት ዋና ስራ አስፈጻሚ ተስፋ መንግስቴ (ደ/ር) በበኩላቸው ግብርናውን ለማዘመንና ወደ ሚፈለገው ደረጃ ለማድረስ የሴቶችን እኩልነት፣ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ወሳኝ ነው ብለዋል፡፡

ይህን ለማድረግ ደግሞ የተዘጋጀውን የስትራቴጂ ሰነዱን በሚገባ መመልከትና ክፍተቶችን በመሙላት ተቀባይነት ያለው ሰነድ ሆኖ ከግብርናና ገጠር ልማት ፖሊሲ ጋር ተጣጥሞ ወደ ስራ መግባት እንዳለበት ተናግረዋል፡፡

በግብርና ሚኒስቴር የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳዮች አካቶ ትግበራ ስራ አስፈጻሚ ወ/ሮ ገነት አብደላ የሴቶችን እኩልለነት፣ ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት በግብርናው ዘርፍ ማረጋገጥ ከቻልን የሴቷን አቅም በመፍጠር በዘርፉ ትልቅ ለውጥ የምናመጣበት ነው ብለዋል፡፡

የመድረኩ ተሳታፊዎች ሊካተቱ የሚገባቸውን ሀሳቦች በማንሳት ተወያይተዋል፡፡ በመጨረሻም በግብርና ሚኒስቴር የሚኒስትሩ ጽ/ቤት ኃላፊ ግርማ በቀለ ይህ ሰነድ ዳብሮ እዚህ ደረጃ ላይ እንዲደርስ አስተዋፅዖ ያበረከቱ አካላትንና ስትራቴጂውን በመመልከት ገንቢ አሳባቸውን ያበረከቱ የዩኒቨርስቲ ምሁራንን በማመስገን ቀጣይ ለሚሰሩ ስራዎች አቅጣጫ አስቀምጠዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ካሳሁን ማለቶ

ፎቶግራፍ፡- ዮዲት እንዳለው