FDRE Ministry of Agriculture

በግብርናው ዘርፍ የሚወጡ አዋጆች፣ ደንቦችና መመሪያዎች የዘርፉን ምርታማነት ለማሳደግ ትልቅ አበርክቶ አላቸው፡፡

(አዲስ አበባ፣ ታኀሳስ 17 ቀን 2017 ዓ.ም፣ ግብርና ሚኒስቴር)

የግብርናውን ዘርፍ በማዘመን ሂደት ውስጥ ከሚከወኑ ተግባራት መካከል የዘርፉን የአሰራር ስርዓት አካታችና አሳታፊ በማድረግ የዘርፉን ምርታማነትን ለማሳደግ የሚያግዙ አዋጆች፣ ደንቦችና መመሪያዎችን ማዘጋጀትና ተግባራዊነታቸውን መከታተል እንዲሁም በቀደሙት አመታት ስራ ላይ ውለው የነበሩትን ማሻሻል፣ መሻርና መከለስ አንዱ ተግባር ነው፡፡

እነዚህም አዋጆች፣ ደንቦችና መመሪያዎች አዲሱን የግብርናና ገጠር ልማት ፖሊሲ መሰረት አድርገው በሁሉም የግብርናው የልማት መስኮች ላይ የፖሊሲውን ተፈፃሚነት ለማረጋገጥ የሚረዱ የህግ ማዕቀፎች ናቸው፡፡

በሚኒስቴሩ የህግ አገልግሎት ስራ አስፈፃሚ በለጠ ሰይፉ ግብርና ሚኒስቴር ‘ከማምረት በላይ’ የሚል መሪ ሃሳብ በመያዝ የዘርፉን ምርታማነት ለማሳደግ በትኩረት እየሰራ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

በዚህም አዲስ የፀደቀው የግብርናና ገጠር ልማት ፖሊሲ የዘርፉን ምርታማነት ለማሳደግ አላማ አድርጎ የተነሳ ሲሆን ይህንንም ፖሊሲ ለማስፈፀም የተለያዩ የህግ ማዕቀፎች ተዘጋጅተው ተግባራዊ እየተደረጉ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡

በአሁኑ ወቅትም የግሉ ዘርፍ ባለሃብቶች በግብርና ልማት ስራዎች ላይ በስፋት እንዲገቡ እንዲሁም ምርታማነትን ለማሳደግ እነዚህ አዋጆች፣ ደንቦችና መመሪያዎች የራሳቸው የሆነ አወንታዊ ተፅዕኖ እንደሚናራቸው ስራ አስፈፃሚው አብራርተዋል፡፡

በዚህም ተጠቃሽ የሚሆኑት የግብርና ምርት አምራችና አስመራች አዋጅ፣ የዕፅዋት ዘር አዋጅ፣ የገጠር መሬት አጠቃቀምና አስተዳደር አዋጅ እና የእንስሳት በሽታን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣው ረቂቅ አዋጅ የዘርፉን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ ትልቅ አስተዋፅዖ ይኖራቸዋል ብለዋል፡፡

አዲስ ተሻሽሎ የፀደቀው የገጠር መሬት አጠቃቀምና አስተዳደር አዋጅ ከዚህ ቀደም የነበረውን የአዋጁን ክፍተቶችና የአሰራር ስርዓቶችን በአዲስ እሳቤዎች በመከለስ የመሬት ባለይዞታ የሆነውን አርሶአደር የእርሻ መሬቱን በአግባቡ በመያዝና ለእርሻ ስራ ምቹ በማድረግ የባለቤትነት ስሜትን የሚያዳብር ከመሆኑም ባሻገር ከፋይናንስ ተቋማት ጋር በማስተሳሰር ተጠቃሚ የሚሆኑበትን ዕድል የፈጠረ፣ በይዞታው ላይ ያለውን መብት በውርስ የማስተላለፍ፣ በኪራይና መሰል ስራዎች ተጠቃሚ እንዲሆን ያስቻለ አዋጅ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ከዚህ ቀደም ያልነበረው የግብርና ምርት አምራችና አስመራች አዋጅ፤ አምራቹን እና አስመራቹን በማገናኘት እንዲሁም ለተመረተው ምርት የገበያ ትስስርን በመፍጠር ትልቅ ሚና የሚጫወት አዋጅ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

የዕፅዋት ዘር አዋጅ ከዚህ ቀደም የነበረውን አዋጅ ሙሉ በሙሉ በመሻር እና በመከለስ ተሻሽሎ እንዲቀርብ የተደረገ ሲሆን በዚህም ተግባር በሃገር ውስጥና በውጭ ያሉ የግሉ ዘርፍ አልሚዎች ወደ ልማት እንዲገቡ ትልቅ ዕድል የፈጠረ ነው ብለዋል፡፡

በተመሳሳይም በእንስሳት ዘርፉ ላይ ለበርካታ ዓመታት ስራ ላይ የነበሩ አዋጆች፣ ደንቦችና መመሪያዎችን በአዲስ በመቀየር ተሻሽለው እንዲቀርቡ ታስቦ በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም ገልፀዋል፡፡

የእንስሳት ልየታ፣ ምዝገባና የክትትል ስራዎችን በተቀናጀ አግባብ ለመስራት ተግባራዊ ለማድረግ በተጨማሪም የእንስሳት ጤናና ደህንነትን ለማስጠበቅ የሚያስችል አዳዲስ ሃሳቦችን በማካተት የህግ ማዕቀፍ በማዘጋጀት ለህዘብ ተወካዮች ም/ቤት የግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በማቅረብ ተጨማሪ ግብዓቶችን ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት በማሰባሰብ እና በማዳበር ለውሳኔ እንዲቀርብ እየተጠበቀ እንሚገኝ አውስተዋል፡፡

ስራ አስፈፃሚው አያይዘውም ከዚህ ቀደም በግብርናው ዘርፍ ላይ የወጡ እና በስራ ላይ የሚገኙ አዋጆች፣ ደንቦችና መመሪያዎችን ጊዜውን የዋጀ እና አዳዳስ ሃሳቦችን በማካተት የማስተካከልና የመከለስ ስራዎች በትኩረት እየተሰሩ እንደሚገኙ አብራርተዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ሰለሞን ደምሰው

ፎቶግራፍ፡- ማቲዎስ ተገኝ

#ከማምረትበላይ

#BeyondProduction

—————-

ስለግብርና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፦

ድረ-ገጽ፦ www.moa.gov.et

ፌስቡክ፦ https://www.facebook.com/MoAEthiopia

ዩቲዩብ፦ https://www.youtube.com/@AgricultureEthiopia

ቴሌግራም፦ https://t.me/MoAEthiopianews

ቲዊተር፦ https://x.com/MoA_Ethiopia

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *