FDRE Ministry of Agriculture

በግብርናው ዘርፍ እየተመዘገበ ያለውን ለውጥ ለማስቀጠል የአጋር አካላት ድጋፍ ወሳኝ ነው

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 23/2018 (ግብርና ሚኒስቴር) የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ለስድስት ዓመታት ሲተገበሩ የቆዩ አራት ፕሮጀክቶችን የፌደራልና የክልል የስራ ኃላፊዎች የልማት አጋሮች፣ ከግሉ ዘርፍ እንዲሁም የሌሎች የባለድርሻ አካላት ተወካዮች በተገኙበት ለግብርና ሚኒስቴር አስረክቧል፡፡

ፕሮጀክቶቹ የግብርና የአንድ መስኮት አገልግሎት (Agricultural One Stop Shop)፣ የህብረት ሥራ ላይ የተመሰረተ የዘር ማምረት ፕሮጀክት (Cooperative-Based Seed Production)፣ የግብርና ሜካናይዜሽን አገልግሎት ማዕከላት (Mechanization Service Centres) ፕሮጀክት እና የተቀናጀ ጥልቀት የሌለው የከርሰ ምድር ውሃ መስኖ ልማት ፕሮጀክት (Integrated Shallow Groundwater Irrigation Development) ናቸው፡፡

የግብርና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ሶፊያ ካሳ (ዶ/ር) አራቱም ፕሮጀክቶች የግብርናውን ዘርፍ ለማሻገር ሚናቸው የጎላ መሆኑን በመግለፅ ለፕሮጀክቶቹ ተግባራዊነት ባለድርሻ አካላት ከሚኒስቴር መ/ቤቱ ጎን እንዲቆሙ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ማንደፍሮ ንጉሴ (ዶ/ር) በበኩላቸው መድረኩ በፕሮጀክቶቹ የተገኙ ውጤቶችን ለማስቀጠል፣ ለማስፋትና ወደ ተቋማዊ ስርዓት ለማስገባት የሚያስችል ምዕራፍ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የግብርና የአንድ መስኮት አገልግሎት ፕሮጀክት በግብርና ግብዓት ገበያ ስርዓት ውስጥ ያሉ ወሳኝ ክፍተቶችን ለመፍታት የተቀረፀ ሲሆን አርሶ አደሮች በአንድ ምቹ ቦታ የግብርና ግብዓቶችን የድጋፍና ምክር አገልግሎት ጋር እንዲያገኙ የሚያስችል ነው፡፡

የህብረት ሥራ ላይ የተመሰረተ የዘር ማምረት ፕሮጀክት ዘላቂና ለአርሶ አደር ፍላጎት ተስማሚ የሆነ የዘር ምርት ስርዓት ለመገንባት ያለመ ነው።

በዚህም የህብረት ሥራ ማህበራትና የአካባቢ ዘር አምራቾች የቴክኒክ፣ የተቋማዊና የመሠረተ-ልማት አቅማቸውን እንዲያጠናክሩ ድጋፍ የሚያደርግም ነው፡፡

የግብርና ሜካናይዜሽን አገልግሎት ማዕከላት ፕሮጀክት አነስተኛ አርሶ አደሮች ዘመናዊ የግብርና ማሽነሪዎችን በቀላሉ እንዲያገኙ፣ የሜካናይዜሽን ሥልጠና እንዲወስዱ፣ የጥገናና የመጠገኛ አገልግሎት እንዲጠናከር እና ለግል የሜካናይዜሽን አገልግሎት ሰጪዎች ትክክለኛ መለዋወጫዎች ተደራሽ እንዲሆኑ የተቀረፀ ነው።

የተቀናጀ ጥልቀት የሌለው የከርሰ ምድር ውሃ መስኖ ልማት ፕሮጀክት ደግሞ የከርሰ ምድር ውሃ መስኖ፣ የአየር ንብረት ተስማሚ ቴክኖሎጂዎች፣ የወጣቶች የሥራ ዕድልና ለገበያ የተመሰረተ የግብርና ምርት ስርዓትን የሚያበረታታ ነው፡፡