FDRE Ministry of Agriculture

በጉራጌና በስልጤ ዞን በምግብ ስርዓት ማጠናከሪያ ፕሮግራም በተሰሩ ስራዎች ላይ የመስክ ምልከታ ተደረገ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 9/2019 (ግብርና ሚኒስቴር) የአለም ባንክ እና ሌሎች የልማት አጋር አካላት እንዲሁም የግብርና ሚኒስቴር ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ቡድን በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጉመር እና በስልጤ ዞን አልቾ ውሪሮ ወረዳዎች በምግብ ስርዓት ማጠናከሪያ ፕሮግራም የተከናወኑ የተለያዩ የልማት ስራዎች ላይ ምልከታ አድርገዋል።

የመስክ ምልከታ የተደረገው የኢትዮጵያ የምግብ ስርዓት ማጠናከሪያ ፕሮግራም 6ኛ የጋራ ግምገማ እና የትግበራ ድጋፍ ተልዕኮን መነሻ በማድረግ ነው።

በመስክ ምልከታውም በጉራጌ ዞን ጉመር ወረዳ በምግብ ስርዓት ማጠናከሪያ ፕሮግራም አማካኝነት በወረዳው የተሰሩትን የቁም እንስሳት ግብይት ማዕከል፣ የስርዓተ-ምግብ ተኮር ግብርና ሞዴል መንደር እንዲሁም የወተት መሰብሰቢያ፣ ማቀነባበሪያና ግብይት የህብረት ስራ ማህበር ተጎብኝተዋል።

በተመሳሳይ ቡድኑ በስልጤ ዞን አልቾ ውሪሮ ወረዳ በተደራጁ ወጣቶች የለማ በርካታ ሄክታር የመኸር ሰብል ማሳ፣ በሽልማት ቀበሌ በሞዴል አርሶ አደር ፈዲላ ከማል የተከናወነ የተቀናጀ የግብርና፣ የጓሮ አትክልትና ፍራፍሬ ልማት፣ የአዲስ ገበያ የገበያ ማዕከል እንዲሁም የጠረጋ ከተማ የእህል መጋዘንና በስፍራው ያለውን የገበያ እንቅስቃሴዎ በአካል ተዘዋውሮ ተመልክቷል።

የምግብ ስርዓት ማጠናከሪያ ፕሮግራም በምርጥ ዘር ብዜት በፍራፍሬ፣ ሮዝመሪና ቅመማ ቅመም እንዲሁም በዘመናዊ መስኖ ፕሮጀክት በወረዳው ባከናወናቸው ስራዎች የአርሶ አደሮችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት በዘላቂነት ለማረጋገጥ ትልቅ አበርክቶ ያለው መሆኑን በጉብኝቱ ወቅት ተነስቷል፡፡