የምግብ ስርዓት ማጠናከሪያ ፕሮግራም በድሬዳዋ አስተዳደር የተለያዩ የገጠርና የከተማ ቀበሌዎች ውስጥ ዘመናዊ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም የተለያዩ የልማት ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል፡፡

በአስተዳደሩ የተለያዩ የገጠር ቀበሌዎች ወጣቶችን በማደራጀትና ወደ ልማት በማስገባት በኢጀአነኒ ቀበሌ በፓፓያ ልማት ላይ የተሰማሩ ወጣቶች ፕሮግራሙ ትልቅ እገዛ እንዳደረገላቸው ይመሰክራሉ፡፡
ወጣት አርሶአደር ዑመር አብዱላሂ እና ዑመር አሚን በድሬዳዋ አስተዳደር በኢጀአነኒ የገጠር ቀበሌ ነዋሪ ናቸው፡፡

ወጣቶቹ የክረምት ዝናብን ብቻ በመጠቀም ማሽላ ያመርቱ ስለነበር የሚያገኙት ምርት በጣም አነስተኛ እና ከዕለት ጉርስ የዘለለ አልነበረም፡፡
በዚህም የተነሳ ለተለያዩ ችግሮች ሲጋለጡና የሴፍቲኔት ተረጂ ሆነው ሲኖሩ መቆየታቸውን ያስታውሳሉ፡፡

አሁን ላይ ይህ ሁሉ ታሪክ ተቀይሮ በምግብ ስርዓት ማጠናከሪያ ፕሮግራም በተደረገላቸው ድጋፍ እንዲሁም በተገነባላቸው የመስኖ ግንባታ እና የሶላር ሲስተም አማካኝነት መስኖ በመጠቀም የልማት ስራዎችን እየሰሩ ነው፡፡

በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚደርሱና ከፍተኛ የሆነ ምርት መስጠት የሚችሉ የፓፓያ ምርጥ ዘሮችን ፕሮግራሙ ባደረገላቸው ድጋፍ በ7 ሄክታር መሬት ላይ እያለሙ መሆናቸውንም ወጣቶቹ አብራርተዋል፡፡

እነዚህ ወጣቶች በቀጣይም የእርሻ መሬታቸውን ወደ 27 ሄክታር ለማሳደግና ፓፓያን በኩታ-ገጠም ለማልማት ትልቅ ተስፋን ሰንቀው እየሰሩ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ከተረጂነት ተላቀው ምርታማ መሆን ችለዋል፡፡
በድሬዳዋ አስተዳደር በምግብ ስርዓት ማጠናከሪያ ፕሮግራም ድጋፍ በተለያዩ የገጠር ቀበሌዎች ወጣቶችን በማደራጀት መሬትን እና የተለያዩ የውኃ አማራጮችን በአግባቡ በመጠቀም ትርጉም ያለው ለውጥ እየተመዘገበ መሆኑ የኢጀአነኒ የገጠር ቀበሌ ትልቅ ማሳያ ነው፡፡

አዘጋጅ፡- ሰለሞን ደምሰው
ፎቶግራፍ፡- ያሬድ አሰፋ