(አዲስ አበባ፣ የካቲት 9 ቀን 2018 ዓ.ም፣ ግብርና ሚኒስቴር)
መንግስት ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ለግብርናው ዘርፍ በሰጠው ልዩ ትኩረት አማካኝነት በዘርፉ የተለያዩ የልማት ኢኒሼቲቮች ተቀርፀው ተግባራዊ እየተደረጉ ሲሆን በዚህም በርካታ ውጤቶች እየተመዘገቡ ይገኛሉ፡፡

ከዚህ በተጨማሪም የግብርናውን ዘርፍ ለማዘመን እና ምርታማነትን ለማሳደግ ዘርፉን የሚደግፉ በርካታ ፕሮግራምና ፕሮጀክቶች ተቀርፀው እየተተገበሩ ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ የምግብ ስርዓት ማጠናከሪያ ፕሮግራም (FSRP) አንዱ ነው፡፡

ፕሮግራሙ በድሬዳዋ አስተዳደር የተቀረፁ የግብርና ኢኒሼቲቮችን በመደገፍ ውጤታማ እያደረገ ሲሆን ለአብነትም በአስተዳደሩ የገጠር ቀበሌዎች ውስጥ በንብ፣ በዓሳ ልማት፣ በዶሮ ብዜት፣ በወተት ላሞች ርባታ እና በአትክልትና ፍራፍሬ ልማት እንዲሁም በሌሎች ዘርፈ-ብዙ የልማት ስራዎች ወጣቶችንና ሌሎች የማህበረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ እያደረገ ይገኛል፡፡

የአስተዳደሩ የግብርና፣ ውሃ፣ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ ም/ኃላፊ እና የግብርናና ተፈተጥሮ ሃብት ልማት ፅ/ቤት ኃላፊ ሚስራ አብደላ እንደተናገሩት በአስተዳደሩ ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ ብሎም የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ በርካታ ተግባራት እየተከናወኑና በዚህም አመርቂ ውጤቶች እየተመዘገቡ ነው፡፡

የምግብ ስርዓት ማጠናከሪያ ፕሮግራምም በአስተዳደሩ የተለያዩ የገጠርና የከተማ ቀበሌዎች ውስጥ ዘመናዊ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም የተለያዩ የልማት ስራዎችን እየደገፈ ይገኛል ብለዋል፡፡
በሰብልም በእንስሳት ዘርፉም አዳዲስ ምርጥ ዝርያዎችን ለአርሶአደሩ እንዲደርሱ ከማድረግም ባሻገር የምርምርና ኤክስቴንሽን ስራዎች እንዲጠናከሩ በማድረግ ፕሮግራሙ በርካታ እገዛዎችን እያደረገ እንደሚገኝ ኃላፊዋ አብራርተዋል፡፡

በግብርና፣ ውሃ፣ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ የምግብ ስርዓት ማጠናከሪያ ፕሮግራም ማናጀር አቶ ሲሻው አያሌው በበኩላቸው የአርሶአደሩን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ስራዎችን ፕሮግራሙ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የምግብ ስርዓት ማጠናከሪያ ፕሮግራም በድሬዳዋ አስተዳደር አዳዲስ የግብርና ኢኒሼቲቮችን ውጤታማ እያደረገ መሆኑም ማናጀሩ አክለዋል፡፡

በአስተዳደሩ የተለያዩ የገጠር ቀበሌዎች ወጣቶችን በማደራጀትና ወደ ልማት በማስገባት በኢጀ አነኒ ቀበሌ በፓፓያ ልማት ላይ ተሰማርተው እንዲሰሩ ፕሮግራሙ ትልቅ እገዛ ማድረጉንም ተናግረዋል፡፡
ፕሮግራሙ በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚደርሱና ከፍተኛ የሆነ ምርት መስጠት የሚችሉ የተለያዩ የምርጥ ዘርና ዝርያዎችንም ለአርሶአደሮች እያቀረበ ይገኛል፡፡
ዘጋቢ፡- ሰለሞን ደምሰው
ፎቶግራፈር፡- ያሬድ አሰፋ
#ከማምረትበላይ
#BeyondProduction