(አዲስ አበባ፣ የካቲት 8 ቀን 2017 ዓ.ም፣ ግብርና ሚኒስቴር)
በደቡብ ኮሪያ መንግስት እና በኢትዮጵያ መንግስት የጋራ ትብብር በአዲስ አበባ ቃሊቲ አካባቢ የተገነባው በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነው የግብርና ሜካናይዜሽን የልህቀት ማዕከል በይፋ ተመርቆ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል።
ይህ ማዕከል በሰባት ወራት ውስጥ ተገንብቶ የተጠናቀቀ ሲሆን በማዕከሉም የግብርና ሜካናይዜሽን ማሽነሪዎች ፍተሻ፣ ቁጥጥር፣ ምርምር እና የጥገና ስራዎች የሚከናወኑበት ሲሆን በተጨማሪም በዘርፉ የሰለጠነ የሰው ሃይል ለማፍራት የተለያዩ ሙያዊ ስልጠናዎችም ይሰጡበታል።
በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ የግብርና ሚኒስቴር ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር)፣ የስራና ክህሎት ሚኒስቴር ሚኒስትሩዋ ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል፣ በኢትዮጵያ የኮሪያ አምባሳደር ጃንግ ካንግ፣ በህዝብ ተወካዮች ም/ቤት የግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት እንዲሁም የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል።
የግብርና ሚኒትሩ ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) ሃገራችን ባለ ብዝሃ-ዘርፍ ኢኮኖሚ መከተል ከጀመረችበት ጊዜ ጀምሮ ለግብርናው ዘርፍ ትልቅ ትኩረት እንደተሰጠው ተናግረዋል።
ሚኒስትሩ አያይዘውም ባልፉት ስድስት ዓመታት በዘመናዊ የግብርና ማሽነሪ የሚታረሰውን መሬት ወደ 5 ሚሊዮን ሄክታር ማድረስ እንደተቻለ አብራርተዋል።
ይህ የግብርና ሜካናይዜሽን የልህቀት ማዕከል መገንባቱ ለግብርና ሜካናይዜሽን ዘርፍ ዕድገት አዲስ ምዕራፍ የሚከፍት ነው ያሉት ሚኒስትሩ፣ ለዚህም ግንባታ ድጋፍ ያደረገውን የደቡብ ኮሪያ መንግስትን አመስግነዋል።
በኢትዮጵያ የደቡብ ኮሪያ አምባሳደር ጃንግ ካንግ በበኩላቸው ኢትዮጵያና ደቡብ ኮሪያ የረጅም ጊዜ የሁለትዮሽ ግንኙነት እንዳላቸው ገልፀው የልህቀት ማዕከሉ ግንባታም በትኩረት ስለሰራን በአጭር ጊዜ መጨረስ ችለናል ብለዋል።
ማዕከሉም ለግብርናው ዘርፍ ምርታማነት ትልቅ አበርክቶ እንደሚኖረው አምባሳደር ጃንግ ተናግረዋል።
የግብርና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ሶፊያ ካሳ (ዶ/ር) በግብርና ሜካናይዜሽን ታሪክ የመጀመሪያ የሆነው ይህ የልህቀት ማዕከል የፍተሻ፣ የጥገና፣ የምርምር እንዲሁም የስልጠና ስራዎችን እንደሚያከናውን ተናግረዋል።
የግብርና ሜካናይዜሽን የለህቀት ማዕከል ከደቡብ ኮሪያ መንግስት በተገኘ በ14.7 ሚሊየን ዶላር የተገነባ ነው።
ዘጋቢ፦ ሰለሞን ደምሰው
ፎቶግራፍ፦ ማቲዮስ ተገኝ