ኢትዮጵያ ያላትን የእንስሳት ሀብት ጥቅም ላይ ለማዋል ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ከሌማት ትሩፋት ፕሮግራም ተያይዘው በዝርያ ማሻሻያ፣ በእንስሳት ጤና አገልግሎት፣ በመኖ ልማት፣ በንብ ማነብ፣ በዶሮና ዓሳ ሀብት ልማት ላይ በርካታ ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ፡፡
ይህን እድል እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ከአነስተኛ ከብት አርቢዎች እስከ ታላላቅ ባለሀብቶች በዘርፉ ተሰማርተው እያለሙ ሲሆን ከራሳቸው ተጠቃሚነት አልፈው፣ ሀገራዊ የወተት ምርት እንዲጨምር አስተዋጾ በማበርከትና ለዜጎች የስራ እድል በመፍጠር ውጤታማ ስራን እያከናወኑ ይገኛሉ፡፡ ለዚህም ማሳያ በወተት ላም እርባታ የተሰማሩት በሲዳማ ክልል የሀዋሳ ከተማ ነዋሪ ወ/ሮ ዘሪቱ ታየ ማሳያ ናቸው፡፡
ወ/ሮ ዘሪቱ ታየ በአንድ ወቅት የቤት እመቤት ነበሩ፡፡ ነገር ግን በ1994 ዓ.ም ለስራ ባላቸው ፈቅር በመነሳትና ባለቤታቸውን በገቢ ለመደገፍ የወጠኑት እቅድ ሰምሮላቸዋል፡፡

በዚህም በ1994 ዓ.ም 4 ሺህ ብር ተበድረው አንድ ላም በመግዛት የተጀመረው የከብት እርባታ ስራ ዛሬ ላይ ለወ/ሮ ዘሪቱ መጦሪያ፣ ለልጆቻቸው እና ለብዙዎች የስራ እድል ፈጥረዋል፡፡
ትላንት ከመቀመጥ ብለው የጀመሩት ስራ አሁን ላይ 28 የተሻሻሉ የውጭ ዝርያ የወተት ላሞች ላይ በመድረስ የሀብት ምንጭ መሆን ችሏል፡፡
በዚህም በቀን ከአንድ ላም በአማካይ 20 ሌትር ወተት የሚያገኙ ሲሆን አሁን ባለው የገበያ ዋጋ 1 ሊትር እስከ 120 ብር በሀዋሳ ከተማ እየሸጡ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ አሁን ላይ 5 የወተት ማከፋፈያና እርጎ የሚሸጡበት ቤት በሀዋሳ ከተማ ከፍተው ከልጆቻቸው ጋር እያስተዳደሩት ይገኛሉ፡፡
ለውጣቸውንም ሲያስረዱ ትላንት በእግር እየተንቀሳቀሱ ስራቸውን ይከሁኑ ነበር፡፡ ዘሬ የወተት ምርታቸው በመኪና ወደ መሽጫ ቦታ ይላካል፡፡ ይህም የለውጡ ማሳያ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም ከብት የሚንከባከቡ፣ የሚያልቡና ወተት ለሚሸጡ 27 ዜጎች የስራ እድል በመፍጠር ተጠቃሚ እያደረጓቸው ነው፡፡
የስራ እድል ከተፈጠረላቸው ወጣቶች አስራት ዘለቀ አንዱ ሲሆን በፊት ስራ አጥ እንደ ነበር ነገር ግን በወ/ሮ ዘሪቱ የወተት ላም እርባታ ማዕከል በተፈጠረለት የስራ እድል ገቢ በማግኘት እራሱን እያስተዳደረ መሆኑን ተናግሯል፡፡
የእንስሳት ዘርፉ በደንብ ከተሰራበት ከራስ አልፎ ለሌሎች ዜጎች የስራ እድል በመፍጠር እንዲሁም በምግብ እራስን ለመቻል በሚደረገው ጥረት ውስጥ የሚያበረክተው አስተዋጽዖ የጎላ ነው፡፡
“በወጣትነታችሁ የምታሳዩት ትጋት ነገ ስለሚከፍላችሁ፣ሳይታክታችሁ ጠንክራችሁ ስሩ!” ይህ የወ/ሮ ዘሪቱ ታየ መልዕክት ነው።
