FDRE Ministry of Agriculture

በኩታ-ገጠም የሰብል አመራረት ተጠቃሚነቱን ያረጋገጠ አርሶ አደር!

በኩታ-ገጠም የሰብል አመራረት አርሶ አደሮች ይበልጥ ተጠቃሚ እየሆኑ ይገኛሉ፡፡ በዚህ በዘመናዊ አሰራር አርሶ አደሮች በተደራጀ የምርት ስርዓት በመሳተፍ የግብዓት፣ የቴክኖሎጂ፣ የምክርና የገበያ አገልግሎቶችን በቀላሉ እንዲያገኙ ምቹ ሁኔታ ተፈጥሮላቸዋል።

አርሶ አደሮች በኩታ-ገጠም የሰብል አመራረት ስርዓት በመደራጀት የተሻሻሉ የዘር ዝርያዎችንና ሌሎች ግብዓቶችን በጋራ በመጠቀም የምርት ጥራት እና ምርታማነትን ጨምረዋል።

በቡድን በመሆን የግብዓት ግዥና የምርት ሽያጭ ወጪን መቀነስ፣ የገበያ ድርድር አቅምን ማሳደግ፣ ከአግሮ-ፕሮሰሲንግ ኢንዱስትሪዎችና ከሌሎች ገዢዎች ጋር ቀጥተኛ የገበያ ትስስር መፍጠር እና ገቢያቸውን ማሳደግ ችለዋል። ከግብርና ዘርፍ ባሻገር ለሀገራዊ ኢኮኖሚ እድገትም የበኩላቸውን አስተዋፅዖ እያበረከቱ ይገኛሉ፡፡

ከኩታ-ገጠም የሰብል አመራረት ስርዓት ተጠቃሚ ከሆኑት አርሶ አደሮች መካከል አርሶ አደር አባራያ አባዱላ አንዱ ናቸው፡፡ በኦሮሚያ ክልል ጅማ ዞን ቀርሳ ወረዳ የጌሎ ቀበሌ ነዋሪ ናቸው፡፡ የሰዮ የበቆሎ ኩታ-ገጠም (ክላስተር) አባል ናቸው፡፡

የዛሬ አምስት አመት ነበር 45 አርሶ አደሮች ሆነው በኩታ-ገጠም ተደራጅተው ስራ የጀመሩት፡፡ ዛሬ 144 ሆነው በ133 ሄክታር መሬት ላይ በቆሎን በኩታ-ገጠም እያለሙ ሲሆን ከዚህ ውስጥ አርሶ አደር አባራያ 3 ሄክታር አላቸው፡፡

በዚህ በዘመናዊ የእርሻ አሰራር፣ አርሶ አደር አባራያ ምን ለውጥ አመጡ? አርሶ አደሩ እንደነገሩን፣ በፊት ከአንድ ሄክታር መሬት የሚያገኙት የበቆሎ ምርት ከ30 ኩንታል አይዘልም ነበር፡፡ በኩታ-ገጠም ተደራጅተው ማልማት ከጀመሩ ወዲህ ግን የበቆሎ ምርታማነት በየዓመቱ እየጨመረ መጥቷል፡፡

አምና ከ3 ሄክታር መሬታቸው 160 ኩንታል ያገኙ ሲሆን ዘንድሮ በቆሎው ጥሩ ስለያዘ ከአንድ ሄክታር 70 ኩንታል፣ ከሱስቱ ሄክታር 210 ኩንታል ይጠብቃሉ፡፡

አርሶ አደር አባራያ መኖሪያ ቤታቸውን ከሳር ቤት ወደ ቆርቆሮ ቤት ቀይረዋል፤ በጅማ ከተማም ደረጃውን የጠበቀ ሞኖሪያ ቤት ሰርተው በማከራየት ጥሩ ገቢ ያገኛሉ፡፡

ልጆቻቸውንም በአግባቡ እያስተማሩ ሲሆን ለኖሯቸው መለወጥ ምክንያት የሆነውን ኩታ-ገጠም የሰብል አመራረት ስርዓትን አጠናክረው በመቀጠል ለግብርና ሽግግር የራሳቸውን አሻራ ለማኖር ፅኑ ሀሳብ አላቸው፡፡

ኩታ-ገጠም የሰብል አመራረት በተለያዩ የምርት ዘመናት በኢትዮጵያ ሲተገበር ቆይቷል፤ አመርቂ ውጤትም እያስመዘገበ ይገኛል።

ከቀደሙት የአፈጻጸም ልምዶች የተገኙ ጥንካሬዎችንና ክፍተቶችን ለይቶ በማረም በ2018/19 የምርት ዘመን የተለያዩ ሰብሎችን በሁሉም ክልሎች በኩታ-ገጠም የማልማት ስራን በተጠናከረ መልኩ ለማስፋፋት ትኩረት ተደርጓል፡፡ 16 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በኩታ-ገጠም ለማልማትም ታቅዶ ተግባራዊ እየተደረገ ይገኛል፡፡