FDRE Ministry of Agriculture

በኩታ-ገጠም አሰራር የቅባት ሰብሎችን ምርታማነት ማሳደግ!

የቅባት ሰብሎች በውጭ ምንዛሬ ግኝት ያላቸው አስተዋፅዖ የሚናቅ አይደለም፡፡ ግብርና ሚኒስቴር ኩታ-ገጠም (ክላስተር) የቅባት ሰብል አሰራርን በማስፋፋት ምርታማነትን  እና የኤክስፖርት ምርትን ለማሳደግ ትኩረት አድርጓል፡፡


በዚህ መነሻነት በ2019 የምርት ዘመን በቅባት ሰብሎች (ሱፍ፣ ሰሊጥ እና አኩሪ አተር) 2.34 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በማልማት 37.94 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማምረት ታቅዷል። ከዚህ ውስጥ 1.46 ሚሊዮን ሄክታር በኩታ-ገጠም አሰራር በማልማት 24.68 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማምረት ነው የታቀደው።


በኩታ-ገጠም አሰራር አማካኝነት የቅባት ሰብሎች ምርታማነት ያድጋል፤ የኤክስፖርት ምርትም ይጨምራል፡፡ በዚህ በምርት ዘመኑም የሱፍ ምርታማነት ከ14 ወደ 16፣ የሰሊጥ ከ6 ወደ 7፣ የአኩሪ አተር ደግሞ ከ23 ወደ 24 ኩንታል በሄክታር ለማድረስ በትኩረት ይሰራል።
በተለይም አኩሪ አተር በሀገር አቀፍ ደረጃ የፍላግሺፕ ፕሮግራም በመሆኑ ምርትና ምርታማነቱን በማሳደግ ለአግሮ-ፕሮሰሲንግ ኢንዱስትሪ፣ ለኤክስፖርት ገበያ እና ለአርሶ አደሮች ገቢ ማሻሻያ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶታል።


ዕቅዱንም ለማሳካት በቅባት ሰብሎች የእሴት ሰንሰለት ትንተና በማካሄድ ከምርት እስከ ኤክስፖርት ያሉ ዋና ዋና ማነቆዎች ተለይተዋል። በዚህም መሠረት የግብዓት አቅርቦትን ማሻሻል፣ የድህረ ምርት ብክነትን መቀነስ፣ የጥራት ቁጥጥርን ማጠናከር፣ ከአግሮ-ፕሮሰሲንግና ከኤክስፖርት ገበያ ጋር ያለውን ትስስር ማጠናከር እንዲሁም የተሻሻሉ ዘሮችና ሌሎች ግብዓቶችን በወቅቱ ማቅረብ፣ የኤክስቴንሽን አገልግሎትን ማጠናከር፣ ወቅታዊ የአየር ሁኔታ መረጃና የግብርና ምክረ-ሐሳብ ለአርሶ አደሮች ማድረስ የተቀመጡ የመፍትሄ አቅጣጫዎች ናቸው።


በአጠቃላይ የተቀመጠውን ግብ ለማሳካት ሁሉም ባለድርሻ አካላት በቅንጅት በመስራት ድርሻቸውን በአግባቡ መወጣት ይጠበቅባቸዋል።
አዘጋጅ፡- ሸምሱዲን ዩሱፍ
ፎቶ፡-  ዮዲት እንዳለው

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *