ኢትዮጵያ የአፍሪካ “የውሃ ማማ” መገለጫ የሆኑት ሀይቆች፣ ወንዞች እና ግድቦች ለዓሣ ሀብት ልማት ሰፊ እድሎችን ፈጥረዋል። በተለይም የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ንጋት ሀይቅ እና ሌሎች አዳዲስ ግድቦች የዓሣ ምርትን በእጅጉ ለማሳደግ አዳዲስ አቅም ፈጥረዋል።
ሀገሪቱ ከ200 በላይ የዓሣ ዝርያዎችን የያዘች ሲሆን ከዚህ ውስጥ ከ45 በላይ የሚሆኑት ብርቅዬ ዝርያዎች ናቸው። ሆኖም ከእነዚህ ውስጥ የኢኮኖሚ ጥቅም ላይ የዋሉት ከ20 በመቶ ያነሱ በመሆናቸው ዘርፉ አሁንም ሰፊ የኢንቨስትመንት እድልን የሚፈጥር ነው።

የዓሣ ልማት በቅርብ ዓመታት ፈጣን እድገት እያሳየ ያለ ዘርፍ ነው፡፡ በ2014 ዓ.ም 72 ሺህ ቶን የነበረው ምርት በ2018 ዓ.ም ወደ 307 ሺህ ቶን አድጓል። ምርትና ምርታማነቱን ለማሳደግ በ2018 ዓ.ም ብቻ 16 ነጥብ 5 ሚሊዮን የዓሣ ጫጩቶች በማሰራጨት የምርት መሠረቱን ማጠናከር ተችሏል።
ይህ ውጤት የተመዘገበው በሌማት ትሩፋት ኢኒሼቲቭ ተግባራዊ ስራ ነው፡፡ ሀገሪቱ በዓመት ከ400 ሺህ ቶን በላይ የዓሣ ምርት የማምረት ሰፊ አቅም ስላላት አነስተኛ ዓሳ አርቢዎች እና ባለሀብቶች በዘርፉ ቢሰማሩ የላቀ ተጠቃሚ መሆን ይችላሉ።

በአገር ውስጥ የዓሣ ፍጆታ ፍላጎት ከጊዜ ወደ ጊዜ በፍጥነት እየጨመረ ሲሆን የተለያዩ የዓሳ ዝርያዎች ከአገር ውስጥ ፍጆታ ባለፈ በዓለም አቀፍ ገበያም ከፍተኛ ተፈላጊነት አላቸው። በተለይ ከነጭ ዓሣ የሚገኘው የመንሳፈፊያ ፊኛ በቻይና እና በመካከለኛው ምስራቅ ገበያ ከፍተኛ ዋጋ ያለው ምርት ነው። ይህም በአለም አቀፍ ንግድ ተወዳዳሪ ለመሆን ያስችላል፡፡ ከምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ-መንግስታት (IGAD)፣ ከምስራቅና የደቡብ አፍሪካ የጋራ ገበያ (COMESA) እና ከኬንያ ጋር የሚደረገው ቀጠናዊ ትብብር የዘርፉን የወጪ ንግድ እድል የበለጠ እያስፋፋ ይገኛል።

የዘርፉን አቅም ወደ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ለመቀየር መንግሥት የዓሳ ሀብት ልማት ኢንቨስትመንት ግብዓቶች ከቀረጥ ነጻ ማስገባት፣ የቀረጥ እፎይታ እና ገበያ ላይ ድጋፎችን ያደርጋል። በዚህም ለባለሀብቶች አጋዥ ሆኖ የሚያገለግል የኢትዮጵያ እንስሳትና ዓሣ ሀብት ኢንቨስትመንት መመሪያ የተዘጋጀ ሲሆን የፋይናንስ ተቋማት ለዘርፉ ብድር የሚያመቻቹበት ማዕቀፍ ለመፍጠር እየሰራ ይገኛል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም የ10 ዓመት የዘርፉ መሪ እቅድ፣ የዓሣ ጫጩት ማራቢያ፣ የአንድ አይነት ፆታ ጫጩት ማባዣ እና የፓረንት ስቶክ ማዕከላት ግንባታ እየተካሄደ መሆኑ በቀጣይ የተሻለ የአሳ ምርት ውጤት ማግኘት ያስችላል፡፡
በጠንካራ የመንግስት ድጋፍ፣ ምቹ የፖሊሲ እና መሠረተ ልማት የተደገፈው የኢትዮጵያ ዓሣ ሀብት ልማት የምግብና ስነ-ምግብ ዋስትናን ለማጠናከር፣ የሥራ ዕድል ለመፍጠር፣ የውጭ ምንዛሪ ገቢን ለማሳደግ እና ዘላቂ ኢኮኖሚያዊ እድገትን ለማፋጠን የሚያስችል ሰፊ የኢንቨስትመንት መዳረሻ ነው፡፡
አዘጋጅ፡- ተዋበ ጫኔ
