አዲስ አበባ፣ መስከረም 5/2019 (ግብርና ሚኒስቴር) በኢትዮጵያ የሆርቲካልቸር ዘርፉን ለአየር ንብረት ተስማሚ በሆነ ቴክኖሎጂ፣ በታዳሽ ኃይል እና ዘላቂ የግብርና አሰራሮችን ለማጠናከር እና ለማስፋፋት በ”SNV” የሆርቲ-ላይፍ ግሪን ግሮውዝ ፕሮግራም ሶስተኛ ምዕራፍ የማስጀመሪያ መርሃ ግብር ተካሄደ።
እ.ኤ.አ ከ2016 ጀምሮ ሲተገበር የቆየውን የሆርቲ-ላይፍ ፕሮግራም ስኬቶችን መሰረት በማድረግ 3ኛው ምዕራፍ ታዳሽ ኃይልን ለምርታማነት ማዋል ላይ ትኩረት ያደረገ ሲሆን በመርሃ ግብሩ የመንግሥት ተቋማት፣ የልማት አጋሮች፣ የምርምርና ስልጠና ተቋማት፣ የግሉ ዘርፍና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

በግብርና ሚኒስቴር የሚንስትር ዴኤታ አማካሪ አሊ መሐመድ (ፕ/ር) መንግስት በግብርናው ዘርፍ ከልማት አጋሮች፣ ከግሉ ዘርፍ እና ከአርሶ አደሩ ጋር በመተባበር የግብርና ዘርፉን ለማዘመን፣ ምርታማነትን ለማሳደግ፣ የእሴት ሰንሰለቶችን ለማጠናከር እና የዘርፉን የአየር ንብረት ለውጥ ተጋላጭነት ለመቋቋም ያለውን አቅም ለማጎልበት ሰፊ ማሻሻያዎችና ኢንቨስትመንቶች ተግባራዊ መደረጋቸውን ጠቅሰው በዚህ ውስጥ የሆርቲካልቸር ልማት ትልቅ ትኩረት እንደተሰጠው ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ ለሆርቲካልቸር ልማት ያላትን ምቹ ስነ-ምህዳር በመጠቀም ዘርፉን ለማሳደግ ሰፊ ስራ እየተሰራ መሆኑን የገለፁት ፕሮፌሰር አሊ፣ ይህን ለመጠቀም ከኔዘርላንድ መንግስት ጋር በመተባበር በ”SNV” ኢትዮጵያ ሆርቲ-ላይፍ ፕሮጀክት አማካኝነት በመጀመሪያው እና በሁለተኛው ምዕራፍ ሲሰሩ የቆዩት የዘርፉ ልማቶች ትልቅ ለውጥ አስመዝግበዋል ብለዋል፡፡
በሶስተኛው ምዕራፍ (እ.ኤ.አ 2026-2029) የሚተገበረው አዲስ ኢኒሼቲቭ በ7 ክልሎች የሆርቲካልቸር ምርት ስርዓቶችን በማሻሻል፣ ቴክኖሎጂዎችንና የምርት አሰራር ልምዶችን በማስተዋወቅ እና እሴት ሰንሰለቶችን በማጠናከር ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዲያበረክት ይጠበቃል ብለዋል፡፡
የ”SNV” የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ጁሊ ግራም በበኩላቸው ፕሮጀክቱ በሆርቲካልቸር እሴት ሰንሰለት ውስጥ ታዳሽ ኃይልን በምርታማነት የመጠቀም መፍትሄዎችን በስፋት የሚተገብር መሆኑን ገልፀው ለአየር ንብረት ተስማሚ ግብርናን፣ ታዳሽ ኃይልን፣ የገበያ ትስስርን፣ የፋይናንስ አቅርቦትን እና የአቅም ግንባታን በማቀናጀት ለአርሶ አደሮችና ለገጠሩ ማህበረሰብ ዘላቂ ጥቅም ለማስገኘት እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡
የሚፈለገውን ዘላቂ ጥቅም ለማስገኘትም የባለድርሻ አካላት ትብብር እንደሚያስፈልግ በመርሃ ግብሩ ላይ ተገልጿል፡፡
