FDRE Ministry of Agriculture

በአጭር ጊዜ ውስጥ ትርፋማ የሚያደርገው የዶሮ እርባታ ሥራ  

የዶሮ እርባታ በአጭር ጊዜ ውስጥ አነስተኛ መሬትና ገንዘብን በመጠቀም ከፍተኛ የገቢ ምንጭና የሥራ ዕድል መፍጠር የሚቻልበት ትርፋማ የግብርና ዘርፍ ነው።

በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ (ዶ/ር) የሃሳብ አመንጭነት የተጀመረው የሌማት ትሩፋት ኢኒሼቲቭ በሀገራችን እየጨመረ የመጣውን የዶሮ ሥጋና የዕንቁላል ፍላጎት ለሟላት ሥራውን በዘመናዊ መንገድ ለመምራት እና ለመስራት ትልቅ ዕድል እየፈጠረ ይገኛል፡፡በዶሮ እርባታ ስራ ውጤታማ ለመሆን ከዚህ በታች የተዘረዘሩትን ዋና ዋና ስራዎች መተግበር አስፈላጊ ነው፡፡

የዶሮ እርባታ ዓላማና የዝርያ ምርጫ

በመጀመሪያ በየትኛው የዶሮ እርባታ ስራ ላይ ማተኮር እንዳለን መወሰን ሲሆን በዚህም የዕንቁላል፣ የስጋ ወይም ሁለገብ ዶሮዎችን ለማርባት ለይተን ማወቅ ይጠበቅብናል።
የዕንቁላል ዶሮዎች ከ4 እስከ 5 ወር ዕድሜያቸው ጀምሮ ዕንቁላል መጣል ስለሚጀምሩ እስከ 1 ወይም 2 ዓመት ድረስ ዕንቁላል መስጠት ይችላሉ።
የሥጋ ዶሮዎች በጣም ፈጣን ዕድገት ያላቸው ሲሆን፤ በተመጣጠነ መኖና እንክብካቤ በ45 ቀናት ወይም በ6 ሳምንት ውስጥ ከ2 እስከ 2.5 ኪሎ ግራም ክብደት ደርሰው ለገበያ ይበቃሉ።
ሁለገብ ዶሮዎች፦ ለሥጋም ለዕንቁላልም የሚሆኑ የተሻሻሉ የአካባቢ ዶሮዎች በሽታ የመቋቋም አቅማቸው ከፍተኛ ስለሆነ ለጀማሪዎች ተመራጭ ናቸው።

የጫጩቶች አያያዝ
ጫጩቶች ከ1 ቀን እስከ 4 ሳምንት ባለው ዕድሜያቸው በጣም ደካማና የሰውነት ሙቀታቸውን ማመጣጠን የማይችሉ በመሆናቸው ልዩ እንክብካቤ ያስፈልጋቸዋል።
ጫጩቶቹ በሚያርፉበት ቦታ ላይ የሙቀት አምፖል (መብራት) ወይም የከሰል ምድጃ በማዘጋጀት በቂ ሙቀት መስጠት ይስፈልጋል።
ወደ ቤት እንደገቡ ወዲያውኑ መኖ ከመስጠት በፊት ለስላሳ ለብ ያለ ውሃ በስኳር ወይም በግሉኮስ በጥብጦ በማጠጣት የጉዞ ድካማቸውን መቀነስ ይመከራል።

የቤት አሰራር
የዶሮ ቤት የዶሮዎቹን ጤና፣ ዕድገትና የምርት ጥራት ይወስናል።
ቤቱ የዶሮ ኩስ የሚያመነጨውን መጥፎ የአሞኒያ ጋዝ የሚያስወጣና ንጹህ አየር የሚያስገባ ተደርጎ መሰራት ያለበት ሲሆን ለዚህም የግድግዳው የላይኛው ክፍል በሽቦ የተሸፈነ መሆን ይኖርበታል።
የቤቱ ወለል ከ5 እስከ 7 ሳ.ሜ ውፍረት ያለው የደረቀ ሰጋቱራ ወይም ገለባ ማንጠፍ በወለሉ መርጠብ ዶሮዎቹ በፈንገስና በሳምባ በሽታ እንዳይጠቁ ይከላከላል። ገለባውን በየጊዜው ማገላበጥ ወይም መቀየር ያስፈልጋል።
ለዕንቁላል ዶሮዎች በአንድ ካሬ ሜትር ላይ ከ5 እስከ 6 ዶሮዎች፣ ለሥጋ ደግሞ በአንድ ካሬ ሜትር ከ8 እስከ 10 ዶሮዎች መያዝ እንዲችል ተደርጎ መሰራት ይኖርበታል።

አመጋገብ
ዶሮዎች እንደ ዕድሜያቸውና እንደ ጥቅማቸው የሚሰጣቸው የመኖ ዓይነት ይለያያል።
የመጀመሪያ መኖ፦ ከ1 ቀን እስከ 4 ሳምንት ላሉ ጫጩቶች የሚሰጥ ከፍተኛ ፕሮቲን ያለው መኖ።
የዕድገት መኖ፦ ከ5 ሳምንት እስከ 4 ወር ላሉ ዶሮዎች ለአጥንትና ለአካል ጥንካሬ የሚሰጥ መኖ።
የምርት መኖ፦ ለዕንቁላል ዶሮዎች የዕንቁላል ምርት እንዲጨምሩ እንዲሁም የሥጋ ዶሮዎች ደግሞ በፍጥነት እንዲወፍሩ የሚሰጥ መኖ።
ውሃ፦ ዶሮዎች ዘወትር ንጹህና ቀዝቃዛ ውሃ ማግኘት አለባቸው።

የጤና ቁጥጥርና ጥብቅ የባዮ-ሴኩሪቲ ጥንቃቄ
የዶሮ በሽታ ቤት ውስጥ ከገባ ሙሉ በሙሉ ሊያጠፋ ስለሚችል መከላከያው ክትባትና ንጽህና ብቻ በመሆኑ በአግባቡ ክትባት እንዲያገኙና ቤታቸውን ማጽዳት ይገባል።
የዶሮ እርባታ ስራ በጥንቃቄ እና በትኩረት ከተሰራ በአጭር ጊዜ ውስጥ ትርፋማ የሚያደርግ የስራ ዘርፍ ሲሆን ወጣቶች በማህበር በመደራጀትና በግላቸው ወደ ስራው በመግባት ተጠቃሚነታቸውን ማረጋገጥ ይችላሉ፡፡
በአጠቃላይ የዶሮ እርባታ ስራ ከስራ ዕድል ፈጠራ ባሻገር ለምግብ እና ስነ-ምግብ መረጋገጥ ትልቅ ድርሻ ያለው በመሆኑ ወጣቶች ወደ ዘርፉ ተሰማርተው እንዲሰሩ ሀገራዊ የሌማት ትሩፋት ኢኒሼቲቭ ትልቅ ዕድል እየፈጠረ ይገኛል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *