FDRE Ministry of Agriculture

በአሲዳማነት የተጎዳ የእርሻ መሬትን በማልማት ምርታማነትን ማሳደግ!

የአፈር አሲዳማነት የግብርናን ምርትና ምርታማነት ከሚቀንሱ ምክንያቶች በዋናነት የሚጠቀስ ሲሆን የሚከሰተውም በአብዛኛው የእርሻ መሬትን ባለመንከባከብ ነው።

የአፈርን ለምነት ከሚጎዱ ነገሮች ውስጥ ዋናዎቹ የአፈር መታጠብ፣ ተረፈ ምርትን አሟጦ ከማሳ ላይ ማንሳት፣ ያለ እንክብካቤ መሬትን ደጋግሞ ማረስ፣ የሰብል ንጥረ-ነገሮችን ከአፈር ውስጥ መጨረስ እና ከምክረ ሀሳብ ውጪ የናይትሮጅን ማዳብሪያዎችን መጠቀም ናቸው።

አሲዳማ አፈርን ማከም የሚቻለው በዋናነት በግብርና ኖራ ነው፡፡ በአሲዳማነት የተጎዳውን መሬት በግብርና ኖራ አክሞ ለማልማት ባለፉት አምስት አመታት በርካታ ስራዎች ተከናውነዋል፡፡

ከግብርና ኖራ አቅርቦትና ምርት ጋር በተያያዘ በአማራ፣ ኦሮሚያና ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎች 11 የሚሆኑ የኖራ ወፍጮዎችን በመትከል የግብርና ኖራ እየተመረተ ሲሆን ይህም በአሲዳማነት የተጎዳውን የአርሶ አደሩን የእርሻ መሬት ለማከም ጥቅም ላይ እየዋለ ይገኛል፡፡

በተጨማሪም ከልማት አጋሮች ጋር በመተባበር 5 የግብርና ኖራ ወፍጮዎችን ለመትከል እየተሰራ ነው።

የአሲዳማ አፈር ችግርን በመፍታት ምርትና ምርታማነትን ለመጨመር ግብርና ሚኒስቴር ከተለያዩ የልማት አጋሮች ጋር በመተባበር የንቀናቄ ሰነድ በማዘጋጀት ብዙ ስራዎችን የሰራ ሲሆን ከነዚህም ውስጥ ወደ 1.4 ቢልዮን ብር በመመደብ በክልሎች ትላልቅ ማሳዎች ላይ የግብርና ኖራን በመጠቀም አሲዳማ አፈርን የማክም ሰርቶ ማሳያዎችን በመስራት የግንዛቤ ማስጨበጫና መሰል ስልጠናዎች ከክልል እሰከ ቀበሌ ላሉ ባለሙያዎችና አመራሮች ተሰጥተዋል።

ለዘርፉ በተሰጠው ትኩረት ባልፉት አምስት ዓመታት 103,590 ሄ/ር የእርሻ መሬትን በማከም ወደ ልማት እንዲመለስ ተደርጓል፡፡ ከችግሩ ስፋት አንጻር ግን ብዙ መስራት ስለሚጠበቅ፣ በአሲዳማነት የተጎዳውን መሬት አክሞ ወደ ምርታማነት ለማስገባት ባለድርሻ አካላት ተቀናጅተው በቁርጠኝነት መረባረብ ያስፈልጋል፡፡

አዘጋጅ፡- ካሳሁን ማለቶ

ፎቶ፡- ማቲዎስ ተገኝ