አቶ ገዛኝ መኮንን በኦሮሚያ ክልል ቢሾፍቱ ከተማ የሚኖሩ በወተት ላሞች እርባታ ላይ የተሰማሩ ስኬታማ አርሶና አርብቶ አደር ናቸው።

በሁለት የወተት ላም ስራቸውን የጀመሩት አቶ ገዛኝ በአሁኑ ወቅት 31 የወተት ላሞች ያሏቸው ሲሆን፣ ከእነዚህም ውስጥ ስምንቱ የሚታለቡ ናቸው፡፡ አስራ ሁለቱ ደግሞ ጥጆችን ለመውለድ ቀናቸው ደርሷል።

በቀን በአማካይ 185 ሊትር ወተት የሚያመርቱ ሲሆን፣ ከአንድ ላምም በአማካይ ከ24 እስከ 25 ሊትር ወተት ያገኛሉ፡፡
የሚያመርቱትን ወተት ለአካባቢው ማህበረሰብ እንዲሁም ለአዲስ አበባ ነጋዴዎች ያቀርባሉ፡፡ በዚህም የወተት ላሞች እርባታ ስራ በአካባቢያቸው ለሚገኙ ለአራት ወጣቶችም በቋሚነት የስራ እድል መፍጠር የቻሉ ታታሪ አርሶና አርብቶ አደር ናቸው።

ይህ ስራ ቤተሰባቸውን ለማስተዳደር እና ልጆቻቸውን ለማስተማር እንደረዳቸው የሚገልጹት አቶ ገዛኝ፣ ወደፊት ስራውን በማስፋፋት ወደ ወተት ማቀነባበር (processing) ለመግባት ትልቅ ራዕይ ሰንቀው በትጋት እየሰሩ እንደሚገኙና ከዚህ በተጨማሪም እንደ ምርምር እና ስልጠና ማዕከል አድርጎ ለማሳደግም ፍላጎት አላቸው።
ከክልሉ ግብርና ቢሮ ለተደረገላቸው ድጋፍ ምስጋናቸውን ያቀረቡት አቶ ገዛኝ በአሁኑ ወቅትም በእርባታ ቦታቸው ውስጥ ከተለያዩ አካባቢዎች የሚመጡ የዘርፉ ባለሙያዎች በወተት ላሞች እርባታና አያያዝ እንዲሁም የወተት አመራረት ላይ ስልጠናዎችን እየወሰዱበት ይገኛሉ።

በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የሌማት ትሩፋትን ፐሮግራም በጥቅምት ወር 2015 ዓ.ም በአርባምንጭ ከተማ በይፋ ከተጀመረ ወዲህ በዝርያ መሻሻልና በወተት ምርታማነት ላይ የሚደነቅ ውጤት እየተመዘገበ ሲሆን በዚህም የእንስሳት ዝርያን ማሻሻል፣ በቂ የእንስሳት መኖ ማቅረብ እና የእንስሳት ጤና አጠባበቅ ስራ ላይ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ በመስራት የወተት ምርትና ምርታማነትን የማሳደግ ስራ በሀገር አቀፍ ደረጃ በትኩረት እየተሰራ ይገኛል።
አዘጋጅ፡- ሰለሞን ደምሰው
ፎቶ፡- ተክለመድህን አቻምየለህ
