ቢሾፍቱ፣ ነሐሴ 27/2018 (ግብርና ሚኒስቴር) የግብርና ዘርፍ የ2018 ዓ.ም የስራ አፈጻጸም፣ የ2019 በጀት ዓመት ዕቅድ ውይይት እንዲሁም የግብርና ሚኒስቴር ምርጥ ፈፃሚ ሰራተኞች የእውቅና መስጠት መርሃ-ግብር ተካሂዷል።

የግብርና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ሶፊያ ካሳ እንደተናገሩት በጠጠናቀቀው በጀት ዓመት ከ33.5 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት በተለያዩ ሰብሎች በማልማት ከ1.85 ቢሊዮን ኩንታል በላይ ምርት መሰብሰብ ተችሏል።
ከዚህ ጎን ለጎን ከ20 ሚሊዮን ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ በማቅረብና በማሰራጨት አርሶ አደሮቻችን የተሟላ የግብርና ግብዓት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ተደርጓል ብለዋል።
በእንስሳት ሀብት ልማት ዘርፍም በሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር በርካታ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ያነሱት ሚኒስትር ዴኤታዋ ከ15.8 ቢሊዮን ሊትር በላይ ወተት፣ 427.9 ሺህ ቶን በላይ ማር እንዲሁም 11.7 ቢሊዮን በላይ እንቁላል በማምረት የተመጣጠነ ምግብ አቅርቦትን በማሻሻል ረገድ አበረታች ውጤት መገኘቱን አብራርተዋል።
በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃና በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርም እንዲሁም በተለያዩ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎች በርካታ አመርቂ ውጤቶች መመዝገባቸውን አንስተዋል።
በግብርና ምርት ወጪ ንግድ ዘርፍም ከ4.55 ቢሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ ማግኘት እንደተቻለ የጠቆሙት ዶ/ር ሶፊያ ከዚህም ውስጥ ቡና ከፍተኛውን ድርሻ እንደሚይዝ ተናግረዋል።
በመድረኩም የግብርና ዘርፍ የ2018 ዓ.ም የስራ አፈጻጸም ሪፖርት፣ የ2019 በጀት ዓመት ዕቅድ፣ ብሔራዊ የአቮካዶ ልማት ፕሮግራም፣ የቦር ፍየል ዝርያ ማሻሻያ ኢኒሼቲቭ እንዲሁም የግብርና ቢዝነስ ኩባንያ ላይ ትኩረት ያደረጉ ጽሁፎች ቀርበው ሰፊ ውይይት ተደርጎበታል።
የግብርና ሚኒስቴር፣ የክልል ግብርና ቢሮ እንዲሁም የተጠሪ ተቋማት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በመድረኩ ላይ ተሳትፈዋል።
