(ሐዋሳ፣ ታህሳስ 21 ቀን 2018 ዓ.ም፣ ግብርና ሚኒስቴር)
በበጀት ዓመቱ 600 ሺህ ቶን ቡና ለዓለም ገበያ በማቅረብ 3 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ለማግኘት እየተሰራ መሆኑን የግብርና ሚኒስትሩ አዲሱ አረጋ ተናገሩ።
የግብርና ሚኒስትሩ አዲሱ አረጋ በዛሬው ዕለት በሲዳማ ክልል ሰሜናዊ ሲዳማ ዞን ሸበዲኖ ወረዳ የቡና ልማት እንቅስቃሴ ያለበትን ሁኔታ ጎብኝተዋል።

ባለፉት አምስት ወራት 174 ሺህ ቶን ቡና ወደ ውጪ በመላክ 1 ነጥብ 2 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር ማግኘት እንደተቻለም ሚኒስትሩ በዚሁ ወቅት ተናግረዋል።
አርሶአደሮቻችን የተሻሉ የቡና ዝርያዎችን በመትከል ምርት እና ምርታማነትን ለማሻሻል እንዲሁም ቡናን በጥራት ለማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ እያደረጉ ያለውን እንቅስቃሴ ተስፋን የሚያጭር ነው ብለዋል።

የሲዳማ ክልል እርሻና ተፈጥሮ ሐብት ልማት ቢሮ ኃላፊ መምሩ ሞኬ በበኩላቸው በክልሉ 40 ሺህ ቶን ቡና ለማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህም በአብዛኛው የቡና አብቃይ የክልሉ አካባቢዎች የለቀማ ስራ እየተከናወነ መሆኑን አስረድተዋል።

በክልሉ ከ175 ሺህ ሄክታር በላይ ማሳ በቡና እየለማ መሆኑንም ቢሮ ኃላፊው ጠቁመዋል።

ዘጋቢ፦ ሰለሞን ደምሰው
ፎቶግራፈር፦ ተክለመድህን አቻምየለህ
