አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 17/2018 (ግብርና ሚኒስቴር) በበጀት ዓመቱ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከግብርናው ዘርፍ ከ3 ቢሊዮን ዶላር በላይ ማግኘት እንደተቻለ የግብርና ሚኒስቴር ሚኒስትር አዲሱ አረጋ ተናገሩ።
የ2018 በጀት ዓመት የግብርናው ዘርፍ የዘጠኝ ወራት አፈፃፀም በተገመገመበት ወቅት በዘጠኝ ወራት ውስጥ በግብርናው ዘርፍ ትርጉም ባለው መንገድ በተከናወኑ ተግባራት በርካታ ስኬቶችን ማስመዝገብ እንደተቻለ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

የመስኖ ግንባታ ማስፋፊያን በመተመለከተ ትላልቅ የመስኖ አውታሮች የተገነቡ ሲሆን ይህም በመስኖ የማልማት አቅማችንን በእጅጉ የሚያጠናክር ነው ብለዋል።
ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከ2 ሺህ በላይ ዘመናዊ የግብርና ማሽነሪዎችን ወደ አርሶአደሩ ማሰራጨት እንደተቻለም ሚኒስትሩ አንስተዋል።
በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ የሆኑ ገበያ ተኮር ምርቶችን በጥራትና በብዛት በማምረት ረገድም አበረታች ስራዎች መከናወናቸውን ያብራሩት ሚኒስትሩ፣ በዚህም ከ3 ቢሊዮን ዶላር በላይ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከግብርናው ዘርፍ ብቻ ማግኘት እንደተቻለ ተናግረዋል።

የመስኖ ስንዴን በስፋት ማምረት፣ በሌማት ትሩፋት ኢኒሼቲቭ በተለይም በእንስሳት ዝርያ ማሻሻያ እንዲሁም በተፈጥሮ ሃብት ልማት ዘርፍ በዋናነት በአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ ፕሮግራም ላይ የተሰሩ ስራዎች በውጤት የሚለኩ መሆናቸውን አይተንበታል ብለዋል።
በበጀት ዓመቱ ለአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ እስካሁን ከ8 ነጥብ 1 ቢሊዮን በላይ ችግኞች መዘጋጀታቸውንም አያይዘው ተናግረዋል።

የሚታረሱ የእርሻ መሬቶቻችን ጦም እንዳያድሩ ሁሉም የግብርና ቤተሰብ ርብርብ ማድረግ እንደሚጠበቅበት ሚኒስትሩ አሳስበዋል።
በመድረኩም የግብርና ሚኒስቴር እና የተጠሪ ተቋማት ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች የተገኙ ሲሆን የ2018 በጀት ዓመት የግብርናው ዘርፍ የዘጠኝ ወራት አፈፃፀም ሪፖርት ቀርቦ ሰፊ ውይይት ተደርጎበታል።
ዘጋቢ፦ ሰለሞን ደምሰው
ፎቶ፦ ዮዲት እንዳለው
