FDRE Ministry of Agriculture

በቀጣይ አምስት አመታት የቡና ምርታማነትን አሁን ካለበት በሄክታር 9 ኩንታል ወደ 21 ኩንታል ለማሳደግ እየተሰራነው!

አዲስ አበባ፣ መስከረም 14/2019 (ግብርና ሚኒስቴር) ግብርና ሚኒስቴር የቡና ምርታማነትን በቀጣይነት ለማሳደግ ከሲዳማ፣ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ እና ከደቡብ ኢትዮጵያ ከልሎች ለተውጣጡ የኤክስቴንሽን አገልግሎት ለሚሰጡ ባለሙያዎች የአቅም ማጎልበቻ ስልጠና እየሰጠ ነው፡፡

በሀገር አቀፍ ደረጃ የቡናውን ዘርፍ ምርትና ምርታማነት በማሳደግ ከቡና ወጪ ንግድ የሚገኘውን የውጭ ምንዛሬ ግኝት ከፍ ለማድረግ በመንግስት ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶታል፡፡

ግብርና ሚኒስቴር ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር ሀገራዊ የቡና ልማት ኢኒሼቲቭ በማዘጋጀት በቀጣይ አምስት አመታት ተግባራዊ በማድረግ የቡና ምርታማነትን አሁን ካለበት በሄክታር 9 ኩንታል ወደ 21 ኩንታል በማሳደግ የውጭ ምንዛሪ ግኝታችንን 6 ቢሊዮን ዶላር ማድረስ ትኩረት አድርጓል፡፡

የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ ታጋይ ኑሩ እንደተናገሩት፣ የሀገራችንን የቡና ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ አሁን አለም የደረሰበትን የቡና ልማት ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም የቡና ልማት ኢኒሼቲቭ በመቅረጽ ምርታማነት ማሳደግ አስፈላጊ ነው፡፡

የብና ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ በመንግስት ልዩ ትኩረት እና አቅጣጫ የተሰጠው ጉዳይ መሆኑን ያብራሩት አቶ ታጋይ፣ ከዘልማዳዊ የአመራረት ዘዴ የተላቀቀ የቡና ልማት ስራዎችን ለማከናወን በርካታ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑንም ገልፀዋል።

የግብርና ሚኒስቴር ዴኤታ አማካሪ ፕሮፌሰር አሊ መሐመድ በበኩላቸው ስልጠናው በዋናነት የቡና ልማት ኢኒሼቲቭ ላይ ትኩረት ያደረገ መሆኑን ገልፀው የመስክ ክትትል፣ የሰብል ጥበቃና እንክብካቤ፣ የማዳበሪያ አጠቃቀም፣ የምርት አሰባብሰብ እና ጥራት እንዲሁም ሌሎች በርካታ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ የባለሙያዎች ስልጠና መሆኑን ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን የቡና፣ ሻይና ቅመማቅመም ልማት መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ፈቃዱ ደፈረስ ሃገራችን የአረቢካ ቡና መገኛ መሆኑዋን ገልጸው፣ ከ6 ሚሊዮን በላይ አርሶአደሮችን እንዲሁም ከ30 ሚሊዮን በላይ ዜጎችን ያሳተፈ የልማት ስራ ነው ብለዋል።

ባለፉት አምስት አመታት የቡናውን ዘርፍ ምርታማነትን ለማሳደግ በርካታ ስራዎች ሲሰሩ መቆየቱን ያስታወሱት መሪ ስራ አስፈፃሚው በዚህም ባሳለፍነው በጀት ዓመት በበርካታ የሃገር ውስጥ እና የውጭ ጫናዎችን በመቋቋም በሃገር አቀፍ ደረጃ ሪከርድ የሆነ 3 ነጥብ 3 ቢሊየን ዶላር ገቢ መገኘቱን አውስተዋል።