ልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም በተለያዩ በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ችግሮች ምክንያት ስር ለሰደደ የምግብ ዋስትና ችግር የተጋለጡ ቤተሰቦችን ለመደገፍ በኢትዮጲያ መንግስት እና በአጋር የልማት ድርጂቶች በ1997 ዓ.ም የተጀመረ ፕሮግራም ነው፡፡
በዚህ ፕሮግራም የታቀፉ የህብረተሰብ ክፍሎች በገጠር የሚኖሩና ስር ለሰደደ የምግብ ዋስትና ችግር የተጋለጡ ቤተሰቦች ናቸው። የፕሮግራሙ ተጠቃሚዎች በሁለት የተከፈሉ ሲሆኑ በማህበረሰብ ስራ የሚሳተፉ እና በነጻ ድጋፍ የሚያገኙ ናቸው፡፡
በሶማሌ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት የልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም መጀመሩን ተከትሎ በተለያዩ ስራዎች ላይ አበረታች ውጤቶች ተመዝግበዋል፡፡ በማህበረሰብ ስራ የተጎዱ አካባቢዎች ማገገም ጀምረዋል፤ ተጠቃሚዎች በህዝብ ስራ እንቅስቃሴ አማካኝነት ኑሮን ተቋቁመው በምግብ ራሳቸውን እንዲችሉ የማድረግ ስራዎች ተሰርተዋል፡፡
አቶ መሃመድኑር አብዲ ዳውድ በሶማሌ ክልል የምግብ ዋስትና ፕሮግራም ዋና አስተባባሪ ናቸው፡፡ በክልሉ ልማታዊ ሴፍትኔት ፕሮግራም በ2001 ዓ.ም መጀመሩን ገልጸው በ93 ወረዳዋች ውስጥ የሚተገበርና 1‚627‚132 ተጠቃሚዎች ያቀፈ ፕሮግራም መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ፕሮግራሙ ከአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎችና ከሬንጅላንድ አስተዳደር (የግጦሽ አካባቢዎች) ባሻገር በመሰረተ ልማት በኩል የውሃ ተቋማት፣ የትምርት ቤቶች እና የክሊኒኮች ግንባታ ስራዎችን እየሰራ ነው ብለዋል፡፡
አስተባባሪው አክለውም እነዚህ ስራዎች በቂ ውሃ እንዲኖር፣ የአፈር ለምነት እንዲሻሻል፣ የግብርና ምርት እንዲጨምርና የገበያ አቅርቦት እንዲሻሻል ከማድረጉም ባሻገር የአየር ንብረት ለውጥን በመቋቋም የተመጣጠነ ምግብ ለማገኘት የጎላ ሚና እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡
በክልሉ የጠጎዱ፣ የተራቆቱ፣ የተቦረቦሩና እርጥበት አጠር አካባቢዎች እንዲያገግሙ ለማድረግ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ በመደበኛነት እየተሰራ ይገኛል፡፡ ቀብሪ በያህ እና ቀብሪደሃር ፕሮግራሙ የሚተገበርባቸው ወረዳዎች ሲሆኑ በፕሮግራሙም ለውጥ እያመጡ ይገኛሉ፡፡
በወረዳዎቹ ውስጥ የተመረጡ ገርቢ እና ደነባ ቀበሌዎች በአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ ከዚህ በፊት ጥቅም የማይሰጡ አካባቢዎች ለምነት እንዲጨምር በማድረግ ምርትና ምርታማነት እንዲያድግ ከማድረጉም ባሻገር ለመስኖ ስራ ውሃ በማቆር የአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ስራዎችን ተግባራዊ በማድረግ ላይ ይገኛሉ፡፡
ፕሮግራሙ በኑሮ ማሻሻያ እንቅስቃሴ ውስጥ ለተጠቃሚዎች ብድር በመስጠት ከትናንሽ ሱቅ ስራዎች ጀምሮ በግና በሬ አድልበው ለገበያ በማቅረብ እራሳቸውን እና ቤተሰቦቻቸውን እንዲለውጡ እየተደረገ ይገኛል፡፡ በግብርና ስራ እንቅስቃሴ ውስጥ የማህበረሰቡን የስራ ባህል በማሻሻልም ውጤት ማምጣት ተቸሏል፡፡
ወ/ሮ ኢርዴ ኢብራሂም በቀብሪ በያህ ወረዳ የገርቢ ቀበሌ ነዋሪ ሲሆኑ የልማታዊ ሴፍትኔት ፕሮግራም ተጠቃሚ ናቸው፡፡ ወ/ሮ ኢርዴ እንደገለፁት በፊት ከፍተኛ ችግር ውስጥ ነበሩ፡፡ አሁን የማህበረሰብ ስራ ሰርተው በሚከፈላቸው ክፍያ ቢያንስ በቂ ምግብ ማግኘት ችለዋል፡፡ ፕሮግራሙ ልማት እንድናለማ እና እራሳችንን እንድንቀይር እያገዘን ነው ብለዋል፡፡ በቤተሰብ ኑሮ ማሻሻያ ዘዴ በኩል ብድር ወስደው በጎችን በማደለብ ስራ ላይ ተሰማርተው ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡
ወ/ሮ ሩቅያ ሠይድ አሊ የገርቢ ቀበሌ ነዋሪ ሲሆኑ ከአመታት በፊት በነበረባቸው ድህነት ምክኒያት ፕሮግራሙን መቀላቀላቸውን ገልጸው የልማታዊ ሴፍትኔት ፕሮግራም የቀጥታ ተረጂ ነበርኩ ብለዋል፡፡ አሁን ላይ ከምግብ እጥረት በመላቀቅ ከቤተሰብ ኑሮ ማሻሻያ ብድር ወስደው በአካባቢው አነስተኛ ሱቅ በመክፈት ብድሩን በወቅቱ መልሰዋል፡፡ ለሌሎች ሴቶችም ጠንክረው እንዲሰሩ የማማከር ስራ በመስራት አርአያ መሆን ችለዋል፡፡
ተጠቃሚዋ አክለውም በፕሮግራሙ አማካኝነት በቤተሰብ ደረጃ ኑሯቸውን በማሻሻል ልጆቻቸውን እስከ ዩንቨርሲቲ እንዳስተማሩ ጠቅሰው ከፕሮግራሙ እራሴን ችዬ ለመውጣት/ ለመመረቅ ዝግጁ ነኝ ብለዋል፡፡