FDRE Ministry of Agriculture

በሥርዓተ-ምግብ ተኮር ግብርና አስደናቂ ስኬት ያስመዘገበ ሞዴል መንደር!

ኢትዮጵያ ሰፊ የግብርና እምቅ አቅም እና ለም መሬት ያላት አገር ብትሆንም ለአያሌ ዓመታት የሥርዓተ-ምግብ ጉድለት ትልቅ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፈተና ሆኖባት ቆይቷል። ይህ የአመጋገብ ክፍተት ለሕፃናት መቀንጨር፣ ለክብደት ማነስና ለተላላፊ በሽታዎች የመጋለጥ ዕድልን ያሰፋል፡፡ ለችግሩ መባባስ ዋነነኛው ምክንያት ደግሞ የተሰባጠረ ምግብ አመጋገብ ስርዓት ላይ ግንዛቤ ማነስ ነው።

ይህንን ስር የሰደደ ችግር ለመፍታት ግብርና ሚኒስቴር ስትራቴጂ ቀርጾ “የሥርዓተ-ምግብ ተኮር ግብርና” መርህን በማስተዋወቅ በምዕራብ አርሲ ዞን በሻሸመኔ ወረዳ የወተራ ሞዴል መንደር መፍጠር ተችሏል። መንደሩ ግብርናን ከጤናና ከማኅበራዊ ልማት ጋር በማስተሳሰር የአርሶአደሩን ሕይወት እንዴት መቀየር እንደሚቻል ማሳያ ሲሆን ዋና የትኩረት አቅጣጫም አርሶአደሩ አንድ ሰብል ብቻ ሳይሆን አትክልት፣ ፍራፍሬና ጥራጥሬም እንዲያመርት ማድረግ ነው፡፡

በወተራ ሞዴል መንደር የፕሮገራሙ ምስክርና የለውጥ አምባሳደር መሆን ከቻሉት 65 አባዎራዎች መካከል አርሶአደር ኑሪ ኤሌሞ አንዱ ናቸው። አርሶአደር ኑሪ በጓሯቸው በርካታ የግብርና ምርቶችን በማምረት ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡ አርሶአደሩ አቮካዶ፣ ሙዝ፣ ፓፓያ፣ ማንጎ፣ አፕል፣ ካሮት፣ ቀይስር፣ ጎመን፣ ጥቅል ጎመን፣ ሽንኩርት፣ ዘይቱን፣ ቦለቄ፣ በቆሎ፣ ድንች፣ ዱባ እና ቡና በማምረት አስደናቂ ስኬት አስመዝግበዋል።

አርሶአደሩ ስለ ሥርዓተ-ምግብ የግብርና ምርቶች አመራረትና አዘገጃጀት፣ እንዲሁም ስለ አካባቢ፣ ቤትና የልጆች ንጽህና አጠባበቅ ባላቸው ግንዛቤ አመጋገባቸውንና አጠቃላይ የሕይወት ዘይቤያቸውን ቀይረዋል።

የሥርዓተ-ምግብ ተኮር ግብርና ያመጣው ለውጥ በምግብ ምርት ላይ ብቻ የተወሰነ ሳይሆን በቤተሰብ አስተዳደር እና በጾታ እኩልነት ላይም ትልቅ አዎንታዊ ተፅዕኖ አሳድሯል። አርሶአደር ኑሪ የቤትና የወንድ ሥራ ሳይሉ ከባለቤታቸው ጋር እጅና ጓንት ሆነው የሚሰሩ ሲሆን፣ ማንኛውንም የቤት ውስጥ ወጪና ገቢ ከባለቤታቸው ጋር መክረው ይወስናሉ።

ከሁሉም በላይ፣ ባለቤታቸው በእርግዝናዋ ወቅት ተስማሚና የተመጣጠነ ምግብ እንድታገኝ ልዩ እንክብካቤ የሚያደርጉ ሲሆን የቤተሰቡ አባላት ስድስቱን የምግብ ምድቦችን በዕለት ተዕለት ምግባቸው ውስጥ በማካተት እንዲመገቡ አድርገዋል፡፡ ከችግርም ወጥተው ልጆቻቸውን በአግባቡ በማስተማር ጤናማ ሕይወትን እየመሩ ይገኛሉ።

የወተራ የሥርዓተ-ምግብ ተኮር ግብርና ስኬት የሚያሳየው ረሃብንና የሥርዓተ-ምግብ ጉድለትን ለመዋጋት የሚያስፈልገው ሰፊ መሬት ሳይሆን ቁርጠኝነት፣ ግንዛቤና የተቀናጀ ድጋፍ በቂ መሆናቸውን ነው። በመላው ኢትዮጵያ የሚገኙ የገጠር ቀበሌዎች የወተራ ሞደል መንደር አርአያነትን በመከተል እያንዳንዱ አርሶአደር የሥርዓተ-ምግብ ተኮር ግብርናን መተግበር ይጠበቅበታል።

አዘጋጅ፡- ባህሩ ሰጠኝ

ፎቶ፦ ዮዲት እንዳለው