FDRE Ministry of Agriculture

በምግብ እራስን ለመቻል እየተሰሩ ያሉ ስራዎች በአፋንቦ ወረዳ

የገጠር ልማታዊ ሴፍትኔት ፕሮግራም በርካታ ወጣቶች እራሳቸውን እንዲችሉ እያገዘ ይገኛል፡፡

(አዲስ አበባ፣ የካቲት 26 ቀን 2017 ዓ.ም፣ ግብርና ሚኒስቴር)

የገጠር ልማታዊ ሴፍትኔት ፕሮግራም በ11 ክልሎች በ492 ወረዳዎች የሚገኙ 8 ሚሊዮን ተጠቃሚዎችን አካቶ እየተሠራ ይገኛል፡፡ ከአጠቃላይ የፕሮግራሙ ተጠቃሚዎች ውስጥ 85 በመቶ የሚሆኑት በማህበረሰብ ሥራ ላይ የተሰማሩ ሲሆን 15 በመቶ ቀጥታ ተጠቃሚዎች ናቸው፡፡

በአፋር ክልል የገጠር ልማታዊ ሴፍትኔት ፕሮግራም በ38 ወረዳዎች ላይ ተግባራዊ እየተደረገ ሲሆን በክልሉ ካሉት 515 ሺህ 712 ተጠቃሚዎች መካከል 466 ሺህ 803 ተጠቃሚዎች የማህበረሰብ ስራ ሰርተው የሚደገፉ ናቸው፡፡ በአፋር ክልል የአደጋ ስጋት አመራርና ምግብ ዋስትና ኮሙሽን የልማታዊ ሴፍትኔት ፕሮግራም አስተባባሪ አቶ ከድር ኢብራሂም በፕሮግራሙ በተሰሩ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎች የተጎዱ አካባቢዎች አገግመው መልማታቸውን እንዲሁም ጠፍተው የነበሩ እንስሳትና እጽዋት መመለሳቸውን ተናግረዋል፡፡

አስተባባሪው አክለውም የልማታዊ ሴፍትኔት ፕሮግራም በክልሉ የውሃ እጥረት ያለባቸው አካባቢዎችን በመለየት የውሃ አቅርቦት ስራ ለተጠቃሚዎች እና ለእንስሶቻቸው ገንብቶ እንዲጠቀሙ ማድረጉን፣ የመሰረተ ልማት ግንባታዎችን እንደ ትምርት ቤት፣ የጤና ኬላ እና መንገዶች የመገንባትና የማደስ ስራ መስራቱን አብራርተዋል፡፡

በአውሲለሱ ዞን የአፋንቦ ወረዳ በእንስሳት፣ እርሻና ተፈጥሮ ሃብት ልማት ጽ/ቤት የግብርና ኤክስቴንሽን ቡድን መሪ አቶ መሃመድ ከድር ፕሮግራሙ በወረዳው የመስኖ አውታር ጥገናና ጠረጋ ስራን ጨምሮ እንደ ፕሮሶፊስ ያሉ መጤ አረሞችን የማጥፋት ስራም እንደሚሰራ ገልጸው የህብረተሰቡ የስራ ባህልም እንዲቀየር አድርጎታልም ብለዋል፡፡

በወረዳው ሁመዶይታ ቀበሌ ካለው 90 ሄክታር የሚታረስ መሬት 75 ሄክታር የሚሆነው በሴፍትኔት ተጠቃሚዎች የተያዘ ነው ያሉት አቶ መሃመድ፣ አቅም የገነቡ አንዳንድ ተረጂዎች እራሳቸውን ችለው ከፕሮግራሙ እንደወጡ ተናግረዋል፡፡

በአፋንቦ ወረዳ ሁመዶይታ ቀበሌ በምግብ እራስን ለመቻል በሚደረጉ ጥረት ውስጥ የመስኖ ልማት ስራን በስፋት በማከናወን ይታወቃል፡፡ ለመስኖ ስራ በቂ ውሃና ምቹ የእርሻ መሬት አለው፡

አብዱልቃድር መሃመድ ሁመዶይታ ቀበሌ አርብቶ አደርና ከፊል አርሶ አደር ወጣት ነው፡፡ ወጣቱ በፕሮግራሙ የሚታገዝ ቢሆንም በልማታዊ ሴፍትኔት ድጋፍ በተሰራ የመስኖ አውታር በመጠቀም ሽንኩርት እያለማ ይገኛል፡፡ የመስኖ አውታር ጠረጋ ማድረግን ጨምሮ በአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ ላይ በመሳተፍ እየተከፈለኝ ባለገንዘብ ኑሮዬን እየመራሁ ነው ብሏል፡፡

ለሽንኩርትና በቆሎ ልማት ስራዎቼም ግብዓት እገዛለሁ ያለው ወጣቱ፣ የልማታዊ ሴፍትኔት ፕሮግራም ወደ አካባቢያቸው ከመምጣቱ በፊት ምንም አይነት ስራ እንደማይሰራና የወላጆቹ ጥገኛ እንደነበር ገልጿል፡፡

ዘንድሮ በግማሽ ሄክታር መሬት ላይ ከ200 እስከ 250 ኩንታል የሽንኩረት ምርት እንደሚጠብቅ የተናገረው አብዱልቃድር ከፕሮግራሙ ተመርቆ ለመውጣትም ዝግጁ መሆኑን ተናግሯል፡፡

ወ/ሮ ሃዋ ዩሱፍ አርብቶ አደርና ከፊል አርሶ አደር ሲሆኑ በሁመዶይታ ቀበሌ የልማታዊ ሴፍትኔት ፕሮግራም ተጣቃሚ ናቸው፡፡ በወር 5 አምስት ቀን በመስራት በፕሮግራሙ የሚከፈላቸውን ገንዘብ በቆሎና ማሽላ ያመርቱበታል፡፡ እንደ ሽንኩርትና ቲማቲም ያሉ የጓሮ አትክልቶችንም በጊቢያቸው በማምረት ተጠቃሚ ሁነዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ራቢያ ፈንታው