(ወላይታ ሶዶ፣ ታህሳስ 4 ቀን 2018 ዓ.ም፣ ግብርና ሚኒስቴር)
ጥጥ ባለው ረዥም የእሴት ሰንሰለትና ቅብብሎሽ በቀጥታ እና በተዘዋዋሪ ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል የሚፈጥር ሲሆን በአሁኑ ወቅትም በዓለም አቀፍ ደረጃ ከ250 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ ዕድል እየፈጠረ የሚገኝ የጭረት ሰብል ነው፡፡

ግብርና ሚኒስቴር የጥጥ ምርታማነት ለማሳደግና የአምራቹን ማህበረሰብ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት በርካታ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል።
በዚህም በሃገራችን ጥጥ አምራች ለሆኑ አካባቢዎች ለሚገኙ የልማት ጣቢያ ሰራተኞችና አምራች አርሶአደሮች የጥጥ ልማት ላይ ሙያዊ ስልጠናዎች እየተሰጡ ይገኛሉ።
በዛሬው ዕለትም በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ወላይታ ዞን አባላ አባያ ወረዳ ላይ ከዞኑ የተለያዩ ወረዳዎች የተውጣጡ የልማት ጣቢያ ሰራተኞችና አምራች አርሶአደሮች የልምድ ልውውጥ እንዲሁም የኦርጋኒክ ጥጥ ልማቱ መሬት ላይ ያለበትን ደረጃ ለማየት ታሳቢ ያደረገ የመስክ ጉብኝት ተደርጓል።

በሚኒስቴሩ የጥጥ ዕሴት ሰንሰለት ልማት ዴስክ ሃላፊ ቱሉ ደለለኝ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት የጥጥ ልማቱን ምርታማነት ለማሳደግና የአምራቹን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ብሎም የኢንዱስትሪውን የግብዓት አቅርቦት ለማሳደግ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው።
ጥጥ ከተመረተበት ቦታ ቀጥታ ወደ ጥጥ መዳመጫ ፋብሪካዎች እንዲደርስ የሚያስችል የክትትል ስራዎች በቅንጅት እየተሰሩ መሆኑንም አብራርተዋል።

ዴስክ ሃላፊው አያይዘውም በምርት ዘመኑ 110 ሺህ ሄክታር መሬት በማልማት 1 ነጥብ 9 ሚሊየን ኩንታል የጥጥ ምርት ለማግኝት በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል።
አርሶአደር ማልዳ ማልጃየ በወላይታ ዞን አባላ አባያ ወረዳ የጮካሬ ቀበሌ ነዋሪ ሲሆኑ በወረዳው የግብርና ልማት ዕ/ቤት አመካኝነት በተሰጣቸው ተግባራዊ ስልጠና መሰረት የጥጥ ልማት ስራቸውን እያከናወኑ ነው።
በዚህም በመጀመሪያ ዙር ካለሙት ግማሽ ሄክታር መሬት ላይ ከ4 ኩንታል በላይ የጥጥ ምርት ማግኘት እንደቻሉ ተናግረዋል።
በስልጠናው የቀሰሙት ልምድ ለምርታማነታቸው ትልቅ አቅም እንደፈጠረላቸው አርሶአደር ማልዳ ጠቅሰው፣ በቀጣይም የጥጥ ልማት ስራቸውን ከዚህ በተሻለ ለማስፋፋት ዕቅድ እንዳላቸውም ተናግረዋል።

ቀጣይነት ያለውና ጥራቱን የጠበቀ ኦርጋኒክ የጥጥ ምርት በማምረት በተመጣጣኝ ዋጋ በማቅረብ የጨርቃጨርቅ ኢንዱስትሪውን ለማሳደግ በቅንጅት መስራት ይገባል።
ዘጋቢ፦ ሰለሞን ደምሰው
ፎቶግራፈር፦ ያሬድ አሰፋ
