FDRE Ministry of Agriculture

በሙያ የተደገፈ የመኖ ልማት ለእንስሳት ምርታማነት!

ሐዋሳ፣ ግንቦት 10/2018 (ግብርና ሚኒስቴር) ግብርና ሚኒስቴር የእንስሳት ዘርፉን ምርታማነት ለማሳደግ በመኖ ልማት ላይ ሰፊ ስራዎችን እያከናወነ ሲሆን ከተለያዩ የልማት አጋሮች ጋር በመተባበር በየክልሎቹ የእንስሳት መኖ ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎችን ገንብቶ ወደ ስራ እያስገባ ይገኛል።

ፋብሪካዎቹ በሙሉ አቅም እንዲሰሩና የመኖ አቅርቦት ችግር በዘላቂነት እንዲፈታ በተሻሻለ መኖ አመራረት፣ አያያዝ፣ አዘገጃጀትና አጠቃቀም ላይ ለክልል የስራ ኃላፊዎች፣ ባለሙያዎች እና በመኖ ማቀነባበር ላይ ለተሰማሩ ዩኒየኖች ስልጠና ተሰጥቷል።

በግብርና ሚኒስቴር የሚኒስትር ዴኤታ አማካሪ ደጀኔ ታከለ መኖ ለእንስሳት ምርታማነት ቁልፍ ሚና ስላለው መንግስት የመኖ ችግርን ለመቅረፍ ከፖሊሲና ከህግ ማዕቀፍ ጀምሮ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን በመቅረፅ ልማቱን እያፋጠነ ነው ብለዋል።

በእንስሳትና አሳ ሃብት ልማት ዘርፍ ፕሮጀክት የተገነቡ የመኖ ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎችን ወደ ስራ በማስገባት የመኖ ልማቱን በመጠን፣ በአይነትና በጥራት ተደራሽ ለማድረግ ለተግባሪዎች የአሰራር አቅም መፍጠር እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል።

በሚኒስቴሩ የመኖ ሃብት ልማት መሪ ስራ አስፈጻሚ ሙሉጌታ ጉዲሳ (ዶ/ር) በበኩላቸው የመኖ ችግርን በዘላቂነት ለመፍታት የተመጣጠነ መኖ ማምረት ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰው፣ ለዚህም የመኖ ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎችን በመገንባት ወደ ስራ ማስገባት መጀመሩን ተናግረዋል።

የተገነቡ የመኖ ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎች በሙሉ አቅም እንዲያመርቱ ለማስቻል ከደቡብ ኢትዮጵያ፣ ከማዕከላዊ ኢትዮጵያ፣ ከኦሮሚያ እና ከሲዳማ ክልሎች ለተውጣጡ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች በዶሮና በወተት ላም መኖ አመራረትና አመጋገብ እንዲሁም በምጥን መኖ አያያዝና አጠቃቀም ላይ ግንዛቤ መፍጠር ተችሏል።

ዘጋቢ፡- ተዋበ ጫኔ

ፎቶ፡- ማቲዎስ ተገኝ