አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 2/2018 (ግብርና ሚኒስቴር) ባለፉት አራት ዓመታት እየተተገበረ ያለው የሌማት ትሩፋት ኢኒሼቲቭ የእንስሳት ምርታማነትን በማሳደግ የምግብና ስነ-ምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ፣ ከውጭ የሚገቡ የግብርና ምርቶችን በመተካት፣ የወጭ ምርትን በማሳደግና ሰፊ የስራ እድል በመፍጠር ረገድ ትልቅ ሚና እየተጫወተ ነው፡፡
የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ፍቅሩ ረጋሳ(ዶ/ር) በሌማት ትሩፋት ኢኒሼቲቭ ባለፉት አራት ዓመታት የተገኙ ስኬቶች ላይ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

የሌማት ትሩፋት ኢኒሼቲቭ ከተጀመረ ወዲህ የዘርፉን ልማት ለማሳደግ በተሰሩ ስራዎች የወተት፣ እንቁላልና ዶሮ፣ ማርና የዓሳ ምርታማነትን በከፍተኛ መጠን ማሳደግ መቻሉን ተናግረዋል፡፡
ምርታማነትን ለማሳደግ በዝርያ ማሻሻል፣ በግብዓት ስርጭት፣ በመኖ ልማትና እንስሳት ጤና ላይ ሰፊ ስራ መሰራቱን ሚኒስትር ዴኤታው ገልፀው ኢኒሼቲቩ ከመጀመሩ በፊት በነበረው 2014 ዓ.ም በዝርያ ማሻሻል የነበረው 500ሺ እንስሳት የማዳቀል አቅም ዘንድሮ ደግሞ 4.3 ሚሊዮን ላሞችና ጊደሮች ማዳቀል መቻሉን ሚኒስትር ዴኤታው በመግለጫቸው አንስተዋል፡፡

በዶሮ ጫጩት ስርጭት ኢኒሼቲቩ ከመጀመሩ በፊት በ2014 ዓ.ም 26 ሚሊዮን የአንድ ቀን ጫጩቶች ስርጭት የነበረውን ቁጥር ዘንድሮ 180 ሚሊዮን ማድረስ መቻሉን ተናግረዋል፡፡

በሃገር አቀፍ ደረጃ የአሳ ጫጩት ማባዣ ማዕከላትን አጠናክሮ ወደ ስራ በማስገባትና ዘመናዊ ቀፎ በማሰራጨት ሰፊ ስራ የተሰራ ሲሆን ዘንድሮ የአሳ ጫጩት ስርጭትን 16.5 ሚሊዮን እንዲሁም ዘመናዊ ቀፎን 3 ሚሊዮን ማድረስ ተችሏል፡፡

በሌማት ትሩፋት ምርታማነትን ለማሳደግ በተሰሩ ስራዎች የወተት ምርትን ከነበረበት 7.1 ቢሊዮን ሊትር በዚህ ዓመት 15.7 ቢሊዮን ሊትር ማግኘት መቻሉን የገለፁት ሚኒስትር ዴኤታው የእንቁላል ምርትን ከነበረበት 3.2 ቢሊዮን አሁን ላይ 11.7 ቢሊዮን እንቁላል መደረስ መቻሉን በመግለጫቸው አመላክተዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ የዶሮ ስጋ ምርትን ኢኒሼቲቩ ከመጀመሩ በፊት ከነበረበት 90 ሺ ቶን ዘንድሮ 253ሺ ቶን፣ የማር ምርትን ከ146.7ሺ ቶን ወደ 428 ሺ ቶን እንዲሁም የዓሳ ምርትን ከ72.4 ሺ ቶን ዘንድሮ ወደ 307 ሺ ቶን ማድረስ መቻሉን ዶ/ር ፍቅሩ ተናግረዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ተዋበ ጫኔ
ፎቶ፡- ተክለመድህን አቻምየለህ
