አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 5/2018 (ግብርና ሚኒስቴር) ስንዴ በሕዝቡ የእለት ተዕለት ሕይወት ውስጥ ከፍተኛ ሚና ከሚጫወቱ የሰብል ምርቶች ውስጥ አንዱ ነው።
ለረጅም ዓመታት የሀገር ውስጥ የስንዴ ፍላጎትን ለማሟላት ኢትዮጵያ ስንዴን ከውጭ ስታስገባ ቆይታለች፤ ለዚህም በቢሊዮኖች የሚቆጠር የውጭ ምንዛሬ ማውጣት ግድ ሆኖባታል።
ዛሬ ግን ይህ ታሪክ እየተቀየረ ነው።
የመደመር እሳቤ፤ ፀጋን፣ የሰው ኃይልን፣ ዕውቀትን፣ ውሃን እና ቴክኖሎጂን በማቀናጀት ግብርናን ወደ ዘመናዊ፣ ምርታማና ተወዳዳሪ የልማት ዘርፍ ለመለወጥ መሠረት ሆኗል።
በኦሮሚያ ክልል፣ በምዕራብ አርሲ ዞን የሚካሄደው የስንዴ ክላስተር ልማትም የዚህ ለውጥ ተጨባጭ ምሳሌ ነው፡፡
በምዕራብ አርሲ ዞን ዶዶላ ወረዳ በ45,262 ሄክታር መሬት ላይ ስንዴ በኩታ-ገጠም (ክላስተር) እየለማ ይገኛል።
በአጠቃላይ በምዕራብ አርሲ ዞን 188,798 ሄክታር መሬት ላይ ስንዴ በኩታ-ገጠም (ክላስተር) እየለማ እንደሚገኝ ከዞኑ ግብርና ጽ/ቤት ያገኘነው መረጃ ያሳያል።
