በግብርናው ዘርፍ ምርትና ምርታማነትን ከማሳደግ ባሻገር ስርዓተ-ምግብ ተኮር ግብርናን ዕውን በማድረግ የአመጋገብ ስርዓቱ የተስተካከለ እንዲሁም ጤናማና አምራች የሆነ ማህበረሰብ መፍጠር ጊዜ የማይሰጠው አንገብጋቢ ጉዳይ ነው፡፡

በዚህም ግብርና ሚኒስቴር ከሌሎች የልማት አጋር አካላት ጋር በመተባበር እና በመቀናጀት ስርዓተ-ምግብ ተኮር ግብርናን ዕውን ለማድረግ የሚያስችሉ በርካታ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል፡፡

በግብርና ሚኒስቴር የምግብ እና ሥርዓተ-ምግብ ማስተባበሪያ ፅ/ቤት አማካኝነት ስርዓተ-ምግብ ተኮር ግብርናን ተግባራዊ ለማድረግ ሞዴል መንደሮችን የመመስረት ስራዎችን ትኩረት ተደርጎባቸዋል፡፡

በሀገራችን በተለያዩ ክልሎች በተመረጡ ወረዳዎች ውስጥ የስርዓተ-ምግብ ተኮር ግብርና ሞዴል መንደሮችን በመፍጠር አርሶ/አርብቶ አደሮችን በማሳቸው እንዲሁም በጓሯቸው ስድስቱንም የምግብ ምድቦች እንዲያመርቱና እንዲጠቀሙ በተጨማሪም ከፍጆታ የተረፋቸውን ወደ ገበያ በማውጣት ገቢያቸውን እንዲያሳድጉ የሚያደርግ ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛሉ፡፡

ይህም ተግባር የሰብል ምርታማነትን ከመጨመር ባሻገር በንጥረ-ነገር የበለፀጉ ምግቦችን በመመገብ ጤናማ፣ አምራችና ብሩህ አዕምሮ ያለው ትውልድ ለመፍጠር ትልቅ እገዛ እንዳለው ይታመንበታል፡፡

በሀገር አቀፍ ደረጃ ከመቀንጨር ነፃ የሆነ፣ ጤናማ፣ አምራችና ብሩህ አዕምሮ ያለው ትውልድ ለመፍጠር የስርዓተ-ምግብ ተኮር ግብርና ሞዴል መንደሮችን ስራ ወደ ሁሉም አካባቢ በማስፋፋት ሁለንተናዊ ብልፅግናችንን ማረጋገጥ ይገባናል፡፡
ግብርና ሚኒስቴር
ጥቅምት 2018 ዓ.ም