FDRE Ministry of Agriculture

ሳይንሳዊ የእንስሳት በሽታ አሰሳ እና የመረጃ አያያዝ ስርዓት ለተሟላ የእንስሳት ጤና

ኢትዮጵያ የእንስሳት ጤና አገልግሎት ስርዓትን በማዘመን ጥራትና ተደራሽነትን ታሳቢ አድርጋ እየሰራች ትገኛለች፡፡ ለዚህ ደግሞ አዲሱ የግብርናና ገጠር ልማት ፖሊሲ የእንስሳት ጤና አገልግሎትን ለማሳለጥ ትኩረት ከሰጣቸው የፖሊሲ አቅጣጫዎች መካከል የበሽታ መከላከል፣ መቆጣጠር፣ የመረጃ ቅብብሎሽና ድንበር ዘለል በሽታዎችን ጨምሮ የቅድመ ማስጠንቀቂያ ስርዓት ማዘመን አንዱ ነው፡፡

በዚህ ሂደት ውስጥ የእንስሳት ጤና ኢንስቲትዩት የጤና አገልግሎት ስራዎችን በተሟላ የእንስሳት በሽታ መመርመሪያ ላቦራቶሪዎች በመታገዝ የበሽታ አሰሳና እና የመረጃ አያያዝ ስርዓትን እየሰራ ይገኛል፡፡

አገራችን ካላት የእንስሳት ሀብት በተሻለ ተጠቃሚ መሆን እንድትችል ኢንስቲትዩቱ የበሽታ ስርጭትን፣ የስጋት ደረጃና ሊያደርሱ የሚችሉትን የጉዳት መጠን በአግባቡ በማጥናት የእንስሳት ጤና መረጃን በማደራጀትና በመተንተን ለተጠቃሚ እንዲደርስ እያደረገ ነው።

በበሽታ አሰሳና ቅኝት በአጎራባች አገራት የሚገኙ ነገር ግን በአገራችን ያልተከሰቱ በሽታዎች እንደ የስምጥ ሸለቆ ትኩሳት፣ የወፍ ጉንፋን እና የምስራቅ ዳርቻ ትኩሳት በሽታዎች ላይ እንዲሁም በአገራችን በመደበኛነት የሚገኙ የእንስሳት በሽታዎች እንደ አፍተግር፣ ደስታ መሰል የበጎችና ፍየሎች በሽታ መንስኤዎችን እና የስርጭት ሁኔታ ቁጥጥር ስራ ውጤታማ እንዲሆን የሚያስችሉ መረጃዎችን ማሰባሰብ፣ ማደራጀትና መተንተን ስራ እየተሰራ ይገኛል፡፡

ከበሽታ አሰሳ በተጨማሪ የበሽታ ቁጥጥር ላይ ከእርባታ ጋር ተያይዞ የሚከሰቱ የውርጃ፣ የሳንባ ነቀርሳ እና አይ.ቢ.አር (IBR) በሽታዎችን ሁኔታ በእንስሳት እርባታ እና ማቆያ ጣቢዎች እየሰራ ይገኛል፡፡ ይህም ለአገር ውስጥ ምርታማነትን ከመጨመር ባለፈ ወደ ውጭ የሚላኩ የቁም እንስሳት ተቀባይ አገራት በሚያስቀምጡት መስፈርት መሰረት አለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የላቦራቶሪ ምርመራ በማድረግ የወጭ ንግዱን እየደገፈ ይገኛለ።   

በምስራቅ አፍሪካ ብቸኛ የባዮ ሴፍቲ ደረጃ 3 (Biosefety level 3) መመርመሪያ ላቦራቶሪ ባለቤት የሆነው ኢንስቲትዩቱ አገራችን ያላትን ሰፊ የእንስሳት ሃብት ተጠቅማ ከበሽታ ነጻ ቀጠና (Disease free zone) በመፍጠር ወደ ውጭ ገበያ ለመግባት የምታደርገውን ጉዞ ለማሳለጥ እየሰራ ይገኛል፡፡

በምስራቅ አፍሪካ ደረጃውን የጠበቀ የላቦራቶሪ አቅም የገነባ በመሆኑ በተመረጡ በሽታዎች ላይ ሪፈረንስ ላቦራቶሪ፣ ለድንበር ዘለል በሽታዎች የ FAO supporting laboratory እና ለኮሜሳ የእንስሳት ጤና ሪፈረንስ ላቦራቶሪ ሆኖ እያገለገለ ይገኛል፡፡

አገራዊና ቀጠናዊ የእንስሳት ጤና አገልግሎቶችን የሚሰጠው ኢንስቲትዩቱ በእንስሳት ጤና ዙሪያ ላይ ለአገር ውስጥና ለቀጠናው አገራት ባለሙያዎች ተግባር ተኮር የሆኑ የላቦራቶሪ ምርመራ ቴክኒኮች፣ አሰራር ስርዓቶች እንዲሁም የኢፒዲሞሎጂና መረጃ ትንተና ስልጠናዎችን በተከታታይ በመስጠት የእንስሳት ጤናን በማሻሻል ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በሚደረገው ጉዞ ትልቁን ድርሻ እየተወጣ ይገኛል፡፡

አዘጋጅ፡- ተዋበ ጫኔ

ፎቶግራፈር፡- ጌታቸው ምትኩ