አዳማ፣ መጋቢት 26 ቀን 2018 (ግብርና ሚኒስቴር) የ2018/19 ሀገራዊ የሰብል ልማት ንቅናቄ ዙሪያ የፌደራልና የክልል የስራ ኃላፊዎች በተገኙበት ውይይት ተደርጓል፡፡
“ምርትና ምርታማነት ለምግብ ሉዓላዊነት” በሚል መሪ ሃሳብ የተካሄደው ይህ ሃገራዊ የሰብል ልማት ንቅናቄ መድረክ በዋናነት የሚታረሱ የእርሻ መሬቶችን ቁጥር በመጨመር ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ዋስትናን አልፎም የምግብ ሉዓላዊነታችንን ለማረጋገጥ ትልቅ አቅም የሚፈጥር ነው።

የግብርና ሚኒስቴር ሚኒስትር አዲሱ አረጋ የኮቪድ ወረርሽኝ በአለም ላይ ሲከሰት ኢትዮጵያ ለችግሩ ሳትበገር የግብርና ልማት ስራዎችን አጠናክራ በመቀጠሏ ውጤት መመዝገቡን አስታውሰዋል፡፡

ሚኒስትሩ አያይዘውም በአሁኑ ወቅትም በመካከለኛው ምስራቅ የተከሰተው ግጭት በግብርናው ዘርፍ ላይ አሉታዊ ተፀዕኖ እንዳያሳድር ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ በዕውቀት ሊሰሩ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

ግጭቱ በአለም አቀፍ ደረጃ የአፈር ማዳበሪያ እና የነዳጅ አቅርቦት ላይ የሚፈጥረውን ክፍተት የገለፁት ሚኒስትሩ መንግስት ዓለም አቀፍ ተለዋዋጭ ሁኔታን ታሳቢ በማድረግ አበክሮ እየሰራ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡

የኦሮሚያ ክልል ግብርና ቢሮ ኃላፊ ጌቱ ገመቹ በበኩላቸው፤ ክልሉ ከሌሎች ክልሎች ልምድ በመቅሰም የግብርና ልማት ስራዎችን እያስፋፋ መሆኑን አንስተው የሩዝ ልማትን ከአማራ ክልል ተሞክሮ በመቅሰም ሩዝ ማምረት መቻሉን ለአብነት ጠቅሰዋል፡፡

በመድረኩ የ2018/19 ሀገራዊ የሰብል ልማት ንቅናቄ መነሻ ዕቅድ እንዲሁም የመከላከያ ሚኒስቴር የግብርና ልማት እንቅስቃሴን የሚያስቃኝ ሰነዶች ቀርበው ሰፊ ውይይት ተደርጎበታል፡፡
ዘጋቢ፡- ዮሐንስ ደመቀ
ፎቶ፡- ተክለመድህን አቻምየለህ
