FDRE Ministry of Agriculture

የማሽላ ምርታማነትን ለማሳደግ ትኩረት ተደርጓል!

ማሽላ  ከበቆሎ፣ ከስንዴ እና ከጤፍ ቀጥሎ ለሀገራችን የምግብ ዋስትና በ4ኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ ጠቃሚ ሰብል ነው፡፡  በዘርፈ-ብዙ ጠቀሜታው ደግሞ ተወዳዳሪ የለውም፡፡ በንጥረ ነገር ይዘቱ በካርቦሃይድሬት፣ በፕሮቲን፣ በቫይታሚን አና በማዕድን የበለፀገ፤ ከኢኮኖሚ አንፃር ለምግብ፣ ለእንስሳት መኖ፣ ለግንባታ፣ ለማገዶ እና ለኢንዱስትሪ ግብዓት የሚውል ነው፡፡ እንዲሁም በባህላዊና ማህበራዊ በኩልም የጎላ ፋይዳ አለው፡፡

ግብርና ሚኒሰቴር ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሀገራዊ ጠቀሜታውን ግምት ውስጥ በማስገባት ማሽላ ከብሔራዊ የፍላግሽፕ ፕሮግራሞች ውስጥ አንዱ ሆኖ እንዲካተት አድርጓል፡፡

ግብርና ሚኒስቴር ብሔራዊ አደረጃጀትን ዘርግቶ ከAlliance for a Green Revolution in Africa (AGRA) ጋር በመተባበር ያዘጋጀውን  የማሽላ ፍላግሽፕ ፕሮግራም ሰነድን  ከዘርፉ ከፍተኛ ተመራማሪዎች እና ከባለድርሻ አካላት ጋር  ለመጨረሻ ጊዜ የገመገመ ሲሆን ሰነዱ ፀድቆ ወደ ስራ ሲገባ ተደብቀው የቆዩ የማሽላ ፋይዳዎች በስኬት ጎልተው ይወጣሉ ተብሎ ይታሰባል፡፡

ማሽላ ትኩረት ባልተሰጠው ጊዜ እንኳን ከ2 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በላይ በመሸፈን  25 ሚሊዮን ለሚሆኑ አርሶ አደሮች የገቢ ምንጭና የምግብ ዋስትና የሆነ ሰብል ነው፡፡ ዛሬ ጭምብሉ ተገፎ ቀን ወጥቶለታል፡፡ ደረጃውንም ለመንጠቅ መንደርደር ጀምሯል፡፡

ብሔራዊ የማሽላ ፍላግሽፕ  ፕሮግራም ከ2018 – 2022 ዓ.ም የሚተገበር ሲሆን በፕሮግራሙ መጠናቀቂያ ዓመት ላይ ማሽላ ከፍተኛ እመርታ እንደሚያሳይ የተዘጋጀው ሰነድ አመላክቷል፡፡ ይኸውም አሁን ያለው በሄክታር በአማካይ 29 ኩንታል ምርታማነት  ወደ 50 ኩንታል ያድጋል።  ከአግሮ ኢንዱስትሪ ጋርም ትስስር በመፍጠር ጠቀሜታው እየሰፋ ይሄዳል፡፡ እንዲሁም የኑሮ መሰረታቸውን በማሽላ ላይ ካደረጉ 25 ሚሊዮን   አርሶ አደሮች በተጨማሪ  የ2.5 ሚሊዮን ዜጎችን የምግብ ዋስትና የሚያረጋገጥ፣ በሚፈጠረው የስራ እድል እና ምርታማነት 1.7 ሚለዮን ሰዎችን ከድህነት የሚያወጣ እና የግብርናውን GDP በ5% የሚያሳድግ ይሆናል፡፡

አንዳውም በምርጥ ዘሩ ላይ በአግባቡ ከተሰራ ድርቅና አደጋን ከመቋቋም አቅሙ ጋር ተዳምሮ 1ኛ ደረጃውን ከበቆሎ መቀማቱ አይቀርም፡፡ ማሽላ፣ “ሴትና ማሽላ የሌለበት መኖር አይደለም” የተባለለትን አባባሉንም  ዳግም ያድሳል፡፡

አዘጋጅ፡- ሸምሱዲን ዩሱፍ

#ከማምረትበላይ #BeyondProduction