FDRE Ministry of Agriculture

ማህበረሰቡን ተጠቃሚ እያደረገ ያለው የቦንጋ ምርጥ ዝርያ በግ!

ሀገራዊ የሥጋ፣ ቆዳና ሌጦ ሀብት ምርትና ምርተማነትን ለማሳደግ በተለይም የሥጋ፣ ቆዳ እና ሌጦ መገኛ እንስሳ ዝርያዎችን ማጥናት፣ መለየትና በመረጣ የማባዛት ስራዎችን የማከናወን እና ከክልሎች ጋር በመቀናጀት ማህበረሰብ አቀፍ እርባታ ተቋሞችን የማስፋፋት ስራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ፡፡ በዚህ መሰረት እየተሰራባቸው ካሉት ምርጥ የበግ ዝሪያዎች መካከል የቦንጋ ምርጥ ዝርያ በግ አንዱ ነው፡፡


በቦንጋ ምርጥ ዝርያ አውራ (ወንድ) በግ በአንድ ጊዜ ከ2 እስከ 4 ግልገሎች የሚወለዱ ሲሆን አንድ ጊዜ የተወለዱ ግልገሎችም እኩል ያድጋሉ፤ የሞከተው አውራም ከ75-80 ኪሎ ግራም ይመዝናል፡፡ እነዚህ የቦንጋ ምርጥ ዝርያ አውራን ልዩ ያደርጋሉ፡፡
በደቡብ ምዕራብ ኢትጵያ ክልል ማህበረሰቡ ተደራጅተው የቦንጋ ምርጥ ዝርያ አውራ በጎችን በማስፋፋት ከራሳቸው ተጠቃሚነት ባሻገር ለሀገር ኢኮኖሚ እድገት የራሱን አስተዋፅዖ እያበረከተ ይገኛል፡፡ ለዚህም በክልሉ በአዲዮ ወረዳ ቦቃ ቀበሌ መጀመሪያ የተመሰረተውና በግምባር-ቀደምነት የሚጠቀሰው ቦቃ-ሹታ ማህበረሰብ አቀፍ የቦንጋ ዝርያ ማሻሻያ ማህበር ነው፡፡


ማህበሩ በ2002 ዓ.ም በ47 አባላት ነበር የተቋቋመው፡፡ አሁን የአባላት ብዛት 462 የደረሰ ሲሆን አብዛኛው አባላት ሴቶች ናቸው፡፡ ማህበሩ በዓመት ከ700 በላይ አውራዎችን የማቅረብ አቅም አለው፡፡
ማህበሩ ከቦንጋ ግብርና ምርምር ማዕከል ጋር ተቀናጅቶ የማርባት፣ የማሻሻል፣ የማሰራጨትና ዝርያውን የመጠበቅ ስራ ይሰራል፡፡ በዚህ ሂደት ዝርያውን በሀገር ውስጥ ለማስፋፋት በሚያደርገው ጥረት ልክ ተጠቃሚ ሲሆን የማህበሩ አባላትም እየተጠቀሙ ይገኛሉ፡፡


በተቀመጠው መስፈርት መሰረት አንድ አርቢ 3 እናት በጎች ካሉት የማህበሩ አባል መሆን የሚችል ሲሆን እናት በጎችንም ከቤት ሊኖራቸው ወይም ከገበያ መርጦ ሊገዛ ይችላል፡፡ ዝርያውን ለመጠበቅ ሲባል እናት በጎች የመውለድ ችግር ካለባቸውና ሲያረጁ እንጂ ስለማይሸጡ በምርጥ ዝሪያ አውራ በግ እያራባ የእናት በጎችን ቀጥር መጨመር ይችላል፡፡  ከማህበሩ አባላት መካከል ከ40 እስከ 50 እናት በጎች ያላቸው አርቢዎችም አሉ፡፡
ዝርያው የሚሰራው በአውራው (በወንዱ) ላይ ነው፡፡ በመሆኑም ምርጥ ዝርያ አውራ በጎች በማህበሩ ለአባላት ይታደላሉ፡፡ አንድ አውራ በግ ከ25 እስከ 30 አናት በጎችን እንደሚያጠቃ ታሳቢ ተደርጎ በ1ለ5 ለተደራጁ አርቢዎች ወይም በጎጥ ደረጃ ይሰጣል፡፡


አርቢው በጎች ሲወለዱ ወደ መረጃ ሰብሳቢው ይደውልና ተመዝግበው መረጃቸው እንዲያዝ ያደርጋል፡፡ አውራ በጉ ተልዶ 3 ወር ሲሞላው በተቀመጠው መስፈርት መሰረት የዝርያ መረጣ ይደረግና ከተመረጠ ማህበሩ ይገዛዋል፡፡ ለምሳሌ ማህበሩ በ10 ሺህ ብር ይገዛውና ትርፍ ለጋራ ብሎ እስከ 6 ወር ድረስ በደንብ እንዲንከባከበው መልሶ ለአርቢው ይሰጣል፡፡ አርቢውም የመጀመሪያውን ገቢ ያገኛል፡፡
አውራው ለማጥቃት የሚደርሰው ከ6 ወር በኋላ ስለሆነ 6 ወር ሲሞላው ማህበሩ ይቀበለውና ዝርያውን ለሚፈሊጉት አካላት ሽጦ ትርፉን ከአርቢው ጋር ይካፈላል፡፡ ለምሳሌ አንድ አውራ በግ 65 ኪሎ ግራም የሚመዝን ሲሆን አንድ ኪሎ በ800 ብር ሂሳብ 52 ሺህ ብር ቢሸጥ ከተገኘው 42 ሺህ ብር ትርፍ አርቢው 21 ሺህ ብር ያገኛል፡፡


አርቢው 5 አውራ በጎችን በአንድ ጊዜ ማቅረብ ከቻለ ደግሞ በዛው ልክ ተጠቃሚ ይሆናል፡፡ ማህበሩ በየዓመቱ ኦዲት አድርጎ ትርፉን ለአባላቱ ሲያከፋፍልም ድርሻውን ያገኛል፡፡ እንዲሁም ያልተመረጡ አውራዎችን አሞክቶ በመሸጥ ገቢ ያገኛል፡፡ በዚህ መንገድ አንድ አባል አራት ጊዜ ተጠቃሚ ይሆናል፡፡
ከማህበሩ ተጠቃሚ አባላት መካከል አቶ ሐይለማሪያም ገብሬ አንዱ ናቸው፡፡ ስድስት እናት በጎች እና ሁለት አውራ በጎች አላቸው፡፡ ከላይ በተጠቀሰው መሰረት ከቦንጋ ምርጥ ዝርያ በግ እየተጠቀሙ ይገኛሉ፡፡


ቦቃ-ሹታ ማህበረሰብ አቀፍ የቦንጋ ዝርያ ማሻሻያ ማህበር መጀመሪያ የተቋቋመና ለዩኒየን መመስረትም ፈር ቀዳጅ ነው፡፡ የቦንጋ ምርጥ በግ ሕብረት ሥራ ዩኒየን በ2014 ዓ.ም የተመሰረተ ሲሆን 13 ማህበራትን ይዞ እየሰራ ይገኛል፡፡
የቦንጋ ምርጥ ዝርያ አውራ በግን ከሶማሌ እና አፋር በስተቀር ወደ ሁሉም ክልሎች አሰራጭቷል፡፡ በየአመቱ ከ5000-6000 የአውራ በጎችን ስርጭት በማካሄድ ለአርቢው ማህበረሰብ በማቅረብ ለሀገራዊ ኢኮኖሚ እድገት የበኩሉን አስተዋጽዖ እያበረከተ ይገኛል፡፡ 
የቦንጋ ምርጥ በግ ሕብረት ሥራ ዩኒየን ስራን ይበልጥ ለማጠናከር እና ምርጥ ተሞክሮዎቹን ወደ ሁሉም ክልሎች ለማስፋፋት ሁሉም ባለድርሻ አካላት ተቀናጅተው በቁርጠንነት መስራት አለባቸው፡፡