FDRE Ministry of Agriculture

መኖ ልማት ከእንስሳት ምርታማነት ባለፈ ለስራ እድል ፈጠራ

**********************************************************

የሌማት ትሩፋት ኢኒሼቲቭ የእንስሳት ዘርፉ የዜጎች የምግብና ስነ ምግብ ዋስትናን ማረጋገጥን፣ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን መተካትንና የኤክስፖርት ገቢ ማሳደግን ግብ አድርጎ እየተተገበረ ሲሆን በስራ እድል ፈጠራም መሰረታዊ ለውጥ እያስመዘገበ ይገኛል፡፡ በዚህ ሂደት የእንስሳትና አሳ ዘርፍ ልማት ፕሮጀክት(LFSDP) ትልቅ ድርሻ እየተወጣ ይገኛል፡፡

በእንስሳትና አሳ ሃብት ልማቱ ትልቁ ቁልፍ ጉዳይ የእንስሳት መኖ ነው፡፡ በዚህ ሂደት የሚታየውን የመኖ በተለይም የተመጣጠነ የእንስሳት መኖ ችግር ለመፍታት ወጣቶች ተደራጅተው በአነስተኛና መካከለኛ የእንስሳት መኖ ማቀነባበሪያ ወፍጮዎችና ሚክሰሮች እየሰሩ ይገኛሉ፡፡

ወጣት አስቴር ካንካሾ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ወላይታ ዞን ሁምቦ ወረዳ ነዋሪ ናት፡፡ በእንስሳት ህክምና ሳይንስ ትምህርቷን ከአጠናቀቀች በኋላ ለ2 አመታት ስራ በማፈላለግ ጊዜዋን አሳልፋለች፡፡

ይሁን እንጂ ከመቀጠር ይልቅ በትንሹም ቢሆን የራሷን ስራ መጀመር አስፈላጊነቱን በማመኗ ከጓደኞቿ ጋር በመመካከር በእንስሳት ዘርፍ ላይ ለመሰማራት ቁርጠኛ አቋም ያዘች፡፡ በዚህ ጊዜ ነበር የእንስሳትና አሳ ዘርፍ ልማት ፕሮጀክት ለእነዚህ ወጣቶች ድጋፉን ይዞ ብቅ ያለው፡፡ ወጣቶቹም ያገኙትን አጋጣሚ በዋዛ ፈዛዛ ከማሳለፍ ይልቅ ለእንስሳት ዘርፉ ቁልፍ ጉዳይ በሆነው የእንስሳት መኖ ማቀነባበር ላይ መስራትን መርጠው በማህበር ተደራጁ፡፡

መደራጀት ኃይል ነው የሚለውን መርህ በመከተል አስቴርን ጨምሮ ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የተመረቁ 9 ሴቶችና 6 ወንዶች በጋራ ሆነው አንጆኑዮ የዶሮ መኖ ማቀነባበሪያ ግብይት ህብረት ስራ ማህበርን በ2015 ዓ.ም መሰረቱ፡፡

በዚህ ሂደት የመኖ ማቀነባበሪያ ማሽን ከነሙሉ ግንባታው፣ የስራ ማስጀመሪያ የመኖ ግብዓትና ስልጠናዎችን ከፕሮጀክቱ ያገኙት አስቴርና ጓደኞቿ በአሁኑ ሰዓት ከዶሮ መኖ ባለፈ ለወተት ከብቶችና ለድለባ የሚሆን መኖ በማምረት ተጠቃሚነታቸውን እያረጋገጡ ነው፡፡

“ለእንስሳት ልማት ወሳኝ ጉዳይ በሆነው መኖ ልማት ላይ መሰማራታችን ለእኛም ለሀገራችንም ትልቅ ክብር ነው” የምትለው ወጣት አስቴር፣ የእንስሳት መኖ ችግርን ለመፍታት ከሚያደርጉት ሀገራዊ አስተዋፅኦ በተጨማሪ አማራጭ የስራ እድል በመፍጠር  ኑሯቸውን መቀየር እንደጀመሩ ገልጻለች፡፡

የመኖ ማቀነባበር ስራ በእንስሳት ልማት ዘርፉ ዘላቂና አዋጭ ቢዝነስ በመሆኑ አሁን ላይ የማህበሩ አባላት ከቤተሰብ ተረጂነት ተላቀው ሌሎችን ወደ ማገዝ እየተሸጋገሩ ይገኛሉ፡፡ ይህም ተስፋን ሰንቀው በቀጣይ ስራውን ለማስፋፋት መነቃቃትን ፈጥሮላቸዋል፡፡

በከተማና ከተማ ዙሪያ ለሚተገበር የወተትና ዶሮ ልማት የመኖ አማራጭ መፍጠር የቻሉት ወጣቶቹ፣  የመኖ ምርታቸውን ለአካባቢው አርሶአደሮችና ለተለያዩ የዶሮ ማህበራት ያቀርባሉ፡፡ ከዚህ ባለፈ ለሌሎች ወረዳዎችና የክልሉ ዞኖች መኖ በማቅረብ የገበያ ትስስርን ፈጥረዋል፡፡

የመኖ ማቀነባበሪያ ማሽኑ በሰዓት 20 ኩንታል መኖ የማምረት አቅም ያለው ሲሆን በቀጣይ ሙሉ አቅሙን ተጠቅመው በስፋት በማምረት የገበያ ተደራሽነታቸውን ለማስፋት ትኩረት አድርገዋል፡፡

አዘጋጅ፡- ተዋበ ጫኔ

ፎቶግራፈር፡- ዮዲት እንዳለው

#ከማምረትበላይ #BeyondProduction