FDRE Ministry of Agriculture

ልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም ያመጣው ለውጥ ምንድነው?

የልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም በ1997 ዓ.ም ሲጀመር  በዋናነት ዓላማ አድርጎ የተነሳው  የምግብ ክፍተት በመሙላት የቤተሰብ ጥሪት እና የወል ጥሪት መገንባት ነው፡፡ ትኩረት አድርጎ የሚሰራባቸውም አካባቢዎች ለድርቅ ተጋላጭ የሆኑ፣ በተከታታይነት የዝናብ እጥረት ያለባቸው እና የምርት መቀነስ  የሚታይባቸው አካባቢዎች ላይ ሲሆን ፕሮግራሙ የሚያካትታቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ደግሞ የደሀ ደሀ ሆነው ለአደጋ ስጋት የተጋለጡትን ነው፡፡

በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሐረርጌ ዞን በሀብሮ ወረዳ ግብርና ጽ/ቤት  የምግብ ዋስትና ፕሮግራም የስራ ሂደት ባለቤት አቶ አፈንዲ አህመድ ልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም በወረዳው የምግብ ክፍተት ከመሙላት ባሻገር የቤተሰብ ጥሪት በመገንባትና የተጎዱ አካባቢዎች አገግመው እንዲለሙ በማድረግ  ተጨባጭ ለውጥ ማምጣቱን ተናግረዋል፡፡

በቤተሰብ ኑሮ ማሻሻያ ዘዴ በኩል ሁኔታውን በማመቻቸት  የፕሮግራሙ ተጠቃሚዎች ብድር እንዲያገኙ ይደረጋል ያሉት አቶ አፈንዲ፣ በተበደሩት ብር ዶሮዎችና ፍየሎችን ገዝተው በማርባትና አደልበው በመሸጥ ወደ ከብትም ቀይረው ኑሯቸውን እንዳሻሻሉ ገልፀዋል፡፡ የማህበረሰብ ስራ ሰርተው ከሚጠቀሙ 19,353 ተጠቃሚዎች ውስጥ በተለያዩ ድጋፎች  ሀብት  በማፍራት መስፈርቶችን ያሟሉ 74%  ዘንድሮ ለመመረቅ ዝግጁ ሆነዋል ብለዋል፡፡

በካፒታል በጀት በወረዳው በርካታ የመሰረተ-ልማት ስራዎች ተሰርተዋል፡፡ የዌኒ ቀሎ ቀበሌ ነዋሪዎች ለከፍተኛ የመጠጥ ውሃ ችግር ተጋልጠው ውሃ ፍለጋ እስከ 8 ኪሎ ሜትር ስለሚጓዙ ችግሩን ለመፍታት  150 ሜትር ኩብ ውሃ የመያዝ አቅም ያለውና በ3.8 ሚሊዮን ብር የተሰራው የመጠጥ ውሃ ማጠራቀሚያ፣ ውሃውን ወደ ማጠራቀሚያ የሚያስገባ የቱቦ  ዝርጋታና  ከማጠራቀሚያው ወደ ቦኖዎች ወሃ ማስተላለፊያ  መስመር ዝርጋታ ስራዎች ለአብነት ተጠቅሰዋል፡፡

በተለይ በቦራ ቀበሌ በዝናብ እጥረት ምክንያት በየአመቱ ሰብል ይበላሽ ስለነበር ፕሮግራሙ የመስኖ ካናል ዘርግቶ የቀበሌው ማህበረሰብ መስኖ በመጠቀሙ ችግሩ በዘላቂነት መፈታቱን አቶ አፈንዲ ተናግረዋል፡፡

በማህበረሰብ ስራዎች በፊት እጅግ የተጎዱ  አካባቢዎች ለምተው በደን በመሸፈናቸው ዝናብ መሻሻሉን፣ የአፈር መሸርሸር መቆሙን፣ ምንጮች ጎልብተው ከመጠጥ አልፈው ለመስኖ እየዋሉ መሆናቸውን የጠቀሱት አቶ አፈንዲ፣ በዚህም የአርሶ አደሩ ምርትና ምርታማነት ጨምረዋል ብለዋል፡፡

በሀብሮ ወረዳ ውስጥ በፕሮግራሙ ስራዎች አገግመው ከለሙ አካባቢዎች መካከል በኢፋ ገመቹ ቀበሌ ውስጥ የሚገኘው  መንዲሳ (Mandhiisaa) ተፋሰስ አንዱ ነው፡፡ የአካባቢው ነዋሪዎች እንደገለፁት ተፋሰሱ በፊት እጅግ ተጎድቶ በመራቆቱ ማህበረሰቡ ለከፋ ችግር ተጋልጦ ነበር፡፡ ከፍተኛ የዝናብ እጥረት ነበር፤ ጋራው ሙሉ ለሙሉ ወደ ገላጣነት በመቀየሩ የነበረውም ዝናብ በዘነበ ቁጥር ከጋራው የሚወርደው ጎርፍ በጊርጌው ያሉትን ማሳዎች ጠራርገው ይሄድ ነበር፡፡ ዛሬ ግን ተፋሰሱ በፕሮግራሙ በደንብ ለምቶ በደን ተሸፍኗል፡፡ አረንጓዴ ለብሶ የተመልካችን አይን ይስባል፡፡ ከጋራ ላይ በሚወርደው ጎርፍ የአፈር መሸርሸር ቆሟል፤ የዝናብ ሁኔታ ተሻሽሏል፤ የደረቁ ምንጮች ፈልቀው የነበሩም ጎልብተዋል፡፡ ተፋሰሱ በደኑ ለንብ ማነብ፣ በሚያበቅለው ሳር ለከብት እርባታና ማደለብ ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል፡፡ የአካባቢው አርሶአደሮች ከተፋሰሱ ትሩፋት ተቋዳሽ ሆነዋል፡፡

አርአደር ፋይዛ ሁሴን የኢፋ ገመቹ ቀበሌ ነዋሪ ናቸው፡፡ በፊት ምንም ስለሌላቸው የድሃ ድሃ መስፈርትን በማሟላት ነበር በፕሮግራሙ የታቀፉት፡፡ አርሶአደር ፋይዛ እንደነገሩን የማህበረሰብ ስራ ሰርተው በሚያገኙት ክፍያ የምግብ ክፍተታቸውን መሙላት ችለዋል፤ ያገኙትን ድጋፍ ተጠቅመው የተለያዩ ሰራዎችን በመስራት ገቢ ማግኘት ችለዋል፡፡ የቁጠባ ባህላቸውንም አሻሽለዋል፡፡ ባለ 60 ዚንጎ ቆርቆሮ ቤት በመስራት ኑሯቸውን እየቀየሩ ይገኛሉ፡፡

አርአደር ፋይዛ በቤተሰብ ኑሮ ማሻሻያ ዘዴ በኩል የተፈጠረውን ምቹ ሁኔታ ተጠቅመው በተበደሩት ብር 2 ዶሮዎችን ገዝተው ማርባት ጀመሩ፡፡ ከዶሮዎች ባገኙት ገቢ ፍየሎችን ገዝተው ማርባትና አደልበው መሸጥ ቀጠሉ፡፡ ወደ ከብት እርባታም ተሸጋግረው ዛሬ 3 ከብቶች አላቸው፡፡ ንብ እርባታም ጀምረዋል፡፡ ወደፊት እነዚህን ስራዎች አጠናክረው  ለመቀጠል እቅድ እንዳላቸው ነው ወ/ሮ ፋይዛ የተናገሩት፡፡

ፕሮግራሙ  የስርዓተ-ምግብ ችግርንም ለመቅረፍ ይሰራል፡፡ ሴት አርሶአደሮች በቡድን በቡድን ተደራጅተው የተመጣጠነ ምግብ መመገብ ያለውን ፋይዳ እንዲገነዘቡ ያደርጋል፡፡  ነፍሰጡር ሴቶች፣ የሚያጠቡ እናቶች እና ህፃናት የተመጣጠነ ምግብ እንዲመገቡ ትምህርት ይሰጣል፡፡  ምን ዓይነት ምግቦችን መመገብ እንዳለባቸው፣ ምግቦችን እንዴት እንደሚያዘጋጁ እና በአንድ ቀን ውስጥ ስንት ጊዜ መመገብ እንዳለባቸው ግንዛቤ ከመፍጠር ባሻገር ለተግባራዊነቱ ሁኔታውን በማመቻቸት ይደግፋል፡፡ ለምሳሌ የተለያዩ ምርጥ ዘሮችን በማቅረብ የተለያዩ አትክልቶችና ፍራፍሬዎችን በጓሯቸው እንዲያለሙ ያደርጋል፡፡ በዚህም አበረታች ውጤት እንዳገኙ ተጠቃሚዎቹ ተናግረዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *