FDRE Ministry of Agriculture

ልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም ከተረጂነት ወደ አምራችነት ለሚደረገው ሽግግር  የድርሻውን እየተወጣ ይገኛል።

————————————————————

ልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም ከመንግስትና ከአለም ባንክ በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ በተለያዩ ሀገሪቱ አከባቢዎች በተፈጥሮ እና በሰው-ሰራሽ አደጋዎች ለከፋ ችግር የተጋለጡ የህብረተሰብ ክፍሎችን የሚደግፍ ልማታዊ ፕሮግራም ነው፡፡ በሂደት የምግብ ክፍተትን ከመሙላት ባሻገር የቤተሰብና የወል ጥሪትን በመገንባት ተጨባጭ ለውጥ እያመጣ ነው፡፡

ፕሮግራሙ ከሚተገበርባቸው ክልሎች ውስጥ አንዱ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ነው፡፡ ክልሉ የበርካታ ፀጋዎች ባለቤት ሆኖ  ሳለ በተረጂነት መቀጠል  የለብትም በሚል ቁጭት ከአመራር እስከ ሕዝቡ ድረስ ከተረጂነት ወደ አምራችነት ለመሸጋገር  ርብርብ እየተደረገ እንድሚ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ጥላሁን ከበደ የገልጻሉ አከለውም  ክልሉ የደሀ ደሀ ሆነው በፕሮግራሙ የታቀፉት ተጠቃሚዎች በፕሮግራሙ በኩል የተደረገላቸውን ድጋፍ እና የተመቻቸላቸው ምቹ ሁኔታን ተጠቅመው የራሳቸውንም ጥረት በማከል ኑሯቸውን እያሻሻሉ እነደሚገኙ ተናግረዋል።

የምግብ ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ በክልሉ ያሉ የተፈጥሮ  ፀጋዎችን የመለየት ሥራ አስቀድሞ መከናወኑን ጠቁመው፤ ክልሉ በተለይም ዓመቱን ሙሉ የሚፈሱ ወንዞች ባለቤት እንደመሆኑ ይህንን ሀብት በመጠቀም ክረምት ከበጋ ከተሠራ በአጭር ጊዜ ውስጥ በምግብ ራስን የመቻል እድል ሰፊ መሆኑን  መግባባት ላይ ተደርሷል ብለዋል። በየትኛውም ጊዜ የሚያጋጥሙ የተፈጥሮና ሰው ሠራሽ አደጋዎችን መቋቋም የሚያስችል አቅም መፍጠር ላይ ሁሉም ባለድርሻ አካል ትኩረት ሰጥቶ እንዲሠራም አቶ ጥላሁን ጥሪ አቅርበዋል ።

በክልሉ በሚገኙ 52 ወረዳዎች ውስጥ ልማታዊ ሴፍትኔት ፕሮግራም ተግባራዊ እየተደረገ ይገኛል፡፡ በተያዘው ዓመት ለ76 ሺ 671 ተጠቃሚዎች አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ  የምግብ ዋስትና ፍላጎቶችን ከመፍታት ባለፈ ችግሮችን በዘላቂነት የሚፈቱ በርካታ የተፋሰስ ልማትና  የመሰረተ-ልማት ስራዎች መሰራታቸው ተጠቅሷል፡፡ የተፋሰስ ማት ትሩፋቶችንም በአግባቡ ከመጠቀም አንጻር የተጠቃሚዎችን ገቢ  ለማሳደግ  የንብ ማነብ እና አነስተኛ የእንስሳት እርባታን ጨምሮ አርሶ አደሮች የተለያዩ ሰብሎችን፣ አትክልትና ፍራፍሬን በማልማት  የቤተሰቦቻቸውን ኑሮ በማሻሻል ላይ እንደሚገኙ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽነር  ጋንታ ጋማአ ገልፀዋል።

በጋሞ ዞን የምዕራብ አባያ ወረዳ ፅህፈት ቤት አደጋ ስጋት አመራር ዘርፍ ሃላፊ አቶ መላኩ ደአ እንደገለፁት በወረዳው  በማህበረሰብ ልማት ሥራ የተሰማሩ 13 ሺ 961 ተጠቃሚዎች አሉ፡፡  በማህበረሰብ ልማት ሥራ ተጠቃሚ የሆኑና እድሜያቸው ከ18 ዓመት በላይ የሆኑ፣ የጤና እና የአቅም ችግር የሌለባቸው ነዋሪዎች በተፋሰስ ልማት ፣ በደንና ችግኝ ልማት፣  መኖ ልማት፣ በመንገድ ሥራ እንዲሠማሩ ተደርጓል። እስከ አሁን በ24 ተፋሰሶች ላይ በተሠራው ሥራ ከ3 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ  ማልማትና ወደ ቀደሞ ይዞታቸው መመለስ ተችሏል።

በተጓዳኝም ህብረተሰቡ በአካባቢው ያሉትን ፀጋዎች በመጠቀም ኑሮውን እንዲያሻሽል ጥረት እየተደረገ ያሉት ኮሚሽነሩ፣ በዚህም አንድ ሺህ 300 አባዎራዎችን በመለየት በተለያዩ ገቢ ማስገኛ ሥራዎች ላይ እንዲሠማሩ መደረጉን ጠቁመው  በተለይም ወረዳው በንብ ማነብ ሰፊ አቅም ያለው በመሆኑ ይህንን በመጠቀም 999 ቀፎችን ለሶስት ቀበሌዎች መሰራጨቱንና ከተፋሰስ ልማት ሥራ ጋር ማስተሳሰር መቻሉን ተናግረዋል።

የቆላ ሙላቶ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት አቶ አራዶር ዳዊት ገሳፊዛ በአባያ ወንዝ ላይ የደን መጨፍጨፍ ያስከተለውን የጎርፍ አደጋ ያጋጠሙትን ያስታውሳሉ። በጎርፍ አደጋ ከብቶችን ካጡ በኋላ  ኑሯቸውን ለማሸነፍ  የቀን ሥራ ጀመሩ። የቁጠባ ባህሉንም አሻሽለው ባገኙት ብር አሁን  ወደ ንግድ ሥራ ለመሸጋገር አቅደዋል።

ልማታዊ ሴፍቲኔት መርሃ ግብር ጊዜያዊ እፎይታ መስጠት ብቻ ሳይሆን ግለሰቦች እና ማህበረሰቦች በራሳቸው አቅም ተግዳሮቶቻቸውን በዘላቂነት እንዲያሸንፉ ማስቻል ነው። ፕሮግራሙ በአቅም ግንባታ፣ በምግብ ዋስትና እና በማህበረሰብ ፅናት ላይ ትኩረት በማድረግ ለበርካታ ኢትዮጵያውያን ቤተሰቦች የተስፋ በር እየከፈተ ነው።

ዘጋቢ፡- ጌዲዮን ነጋሽ

#ከማምረትበላይ

#BeyondProduction

—————-

ስለግብርና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፦

ድረ-ገጽ፦ www.moa.gov.et

ፌስቡክ፦ https://www.facebook.com/MoAEthiopia

ዩቲዩብ፦ https://www.youtube.com/@AgricultureEthiopia

ቴሌግራም፦ https://t.me/MoAEthiopianews

ቲዊተር፦ https://x.com/MoA_Ethiopia

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *